ቀጥታ፡

አሸባሪውን የህወሀት ቡድንን ለመደምሰስ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሐረር ፤ ነሐሴ 13/2013(ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሀት ቡድንን በመደምሰስ የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበር የተጀመረው የድጋፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ አዲስአለም በዛብህ አስታወቁ።
የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።

በጉባኤ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አፈ -ጉባኤዋ እንደተናገሩት፤ የጥፋት ቡድኑ   የተናጥል ተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገሪቱ ላይ የሽብር ሴራውን እያካሄደ ነው።

በዚህም በአፋር እና  አማራ ክልሎች ዜጎች ላይ   ግድያ እና ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ ይህን የጥፋት ድርጊት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አውግዘነዋልብለዋል።

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትም የኢትዮጵያን ሉአላዊነትን ለማስከበር ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር መሰዋዕትነት እየከፈለ መሆኑ ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሀት ቡድንን በመደምሰስ የሀገሪቱን  ሉአላዊነትን ለማስከበር  የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ አዲስአለም በዛብህ ያስታወቁት።

ምክር ቤቱ ጉባኤ ለሶስት ቀናት በሚኖረው ቆይታ  የ2013 በጀት ዓመት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤትና  የጠቅላይ ፍርድ ቤት አፈጻጻም ሪፖርተርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመልክቷል።

እንዲሁም የክልሉ መስተዳድር የ2014 ስራ ዘመን ማስፈጸሚያ በጀት፣ የተለያዩ አዋጆች እና ሹመቶች ላይ በመምከር  እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
በጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በዜጎች ላይ በፈጸመው  ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት መካሄዱንም የኢዜአ ሪፖርተር ከሐረር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም