ቀጥታ፡

የሃገር ፍቅር የሌለው ሰው እምነቱ ሙሉ አይደለም

ሚዛን፤ ነሐሴ 13/2013 (ኢዜአ) የሃገር ፍቅር የሌለውና ሀገር ስትወረር ዝም የሚል ሰው እምነቱ ሙሉ አይደለም የሚዛን አማን ከተማ  የሃይማኖት አባቶች ። 
ኢትዮጵያ በሃይማኖቷ ባህሏና ታሪኳ ጠላትን ስታሸንፍ የቆየች የነጻነት ሀገር መሆኗን  የሃይማኖት አባቶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሸካ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሀዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ቀለመ ወርቅ አጥናፉ እንደተናገሩት፤ ሃይማኖትና ሀገር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።

ምድር ላይ ባልተሰራ ቤት አንኖርም፤ የሰማይ መንግስት ለመውረስ ስራ የምንሰራው ምድር ላይ በመሆኑ ስለ ሀገር ሰላምና ነጻነት መታገል ግዴታ ነው ያሉት።

ግራህን ሲመታ ቀኝህን ስጥ የሚለው ብሂል የሀገር ልዕልናን ለተዳፈረ የሚተረጎም አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ስለ ሀገር መዋጋትን ሃይማኖት እንደማይከለከል አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ታሪኮች ሃይማኖት ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ነጻነቷን ይዛ እንድትኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በአድዋ የክተት ዘመቻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታቦት ይዞ በመውጣት ከእነ ጳጳሱ አድዋ መዝመታቸውን አስታውሰዋል።

እጅ እግር አጣጥፎ ቁጭ ብሎ በጠላት መሞት ጀግንነት አለመሆኑን አመልክተው "ድል በጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን በጸሎትም ጭምር በመታገዝ የሚመጣ ነው" ብለዋል።

ይልቁንም ሀገርህን ለሚወርና ክብርህን ለሚጋፋ ጠላት ጠንካራ ሆኖ መቆም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ለገጠማት ጦርነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገርን ለመጠበቅ ዘውትር ከምታደርገው ጸሎት ባለፈ ከመንግስት ጎን በመቆም በልኳ መጠን ኃላፊነቷን ትወጣለች ሲሉ አብራርተዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን እስልምና ጉዳዮች የትምህርትና ቅስቀሳ ዘርፍ ኃላፊና የዞኑ ሃይማኖት ፎረም ምክትል ሰብሳቢ አባነጋ አብዱል ከሪም በበኩላቸው፤  እንደ ጂሃድ የሀገር ፍቅር የሌለውና ሀገር ሲወረር የማይታገል ሰው ሙሉ እምነት የለውም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን የገጠማት ፈተና አልፎ ድል እስኪገኝ ድረስ መደገፍና መታገል ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።

"እንደ ሃይማኖት አባት እስከ ግንባር በመሄድ እየጸለይን የመከላከያ ሰራዊት ደጀን ብንሆን ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።

ከወትሮ በተለየ መልኩ የጸሎት መርሐ ግብር በመስጊድ እየተከናወነ እንዳለ የተናገሩት አባነጋ አብዱል ከሪም፤ በእስልምና እምነት ውስጥ መንግስትን መስማትና ተገቢውን ምላሽ መስጠት የአማኝ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር ጉዳይ ላይ ሁላችንም ከመንግስት ጎን በመቆም ኢትዮጵያን መታደግ  ይኖርብናል።

"የሃገር ፍቅር የሌለውና ሀገር ስትወረር ዝም የሚል ሰው እምነቱ ሙሉ አይደለም" ሲሉም ሃይማኖት በሀገር ላይ ያለውን አስተምህሮ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም