ቤተ ክርስቲያኗ በሶማሊ ክልል ለተጎዱ እብያተክርስቲያናት እና ሰዎች ድጋፍ የሚያሰባስብ ኮሚቴ አቋቋመች

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በተከሰተው ግጭት ለተቃጠሉ እና ጉዳትእብያተክርስቲያናት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ የሚያሰባስብ ኮሚቴ ማቋቋሟን  ገለጸች። የቤተ ክርስቲያኗ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብዕፁ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሰጡት መግለጫ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በክልሉ በተከሰተው ግጭት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ካህናትን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል። የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸውን ቤተ ክርስቲያናት በመስራት መልሶ ለማቋቋም እንዲሁም ለተጎጂዎች ዕርዳታ ለማድረግ ገንዘብና ቁሳቁስ  የሚያሰባስብ 14 አባላት ያሉት ዐቢይ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ በውጭና በአግር ውስጥ የሚኖሩ ምዕመናን ቤተ ክርስትያናቱን ለማቋቋም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ በሶማሌ ሀገረ ስብከት በተቃጠሉትና ጉዳት በደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት ስም በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000254922898 ገቢ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ጉዳት የደረሰባቸውን ከረሃብ ለመታደግ ደረቅ ምግቦችን ሃያ ኪሎ ግራም በሚይዝ ካርቶን በማሸግ በመንበረ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤት ለተቋቋመው ኮሚቴ እንዲያስረክቡ ጥሪ አቅርበዋል። ለተጎጂዎች የሚላከውን ምግብና አልባሳት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን 300 ኪሎ ግራም ለማጓጓዝ ቃል መግባቱን ብዕፁ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተናግረዋል። የተቃጠሉ ቤተ ክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት የምህንድስና ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ እንደ ተቋቋመ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ የዲዛይን ሥራው ተከናውኖ  በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንደተፈጠረ ኮሚቴው በቦታው ተገኝቶ የጥናት ሥራ እንዲሰራ ይደረጋል ብለዋል። በመልሶ ግንባታው ከምህንድስና ባለሙያዎቹ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በጠቅላይ ጽህፈት ቤት እንዲገኙም ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ሽኩቻ ህዝብ መጎዳት እንደሌለበት የገለጹት ብዕፁ አቡነ ዲዮስቆሮስ ፖለቲከኞች ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም