ቀጥታ፡

ወጣቱ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን አከርካሪ በመስበር ከአባቶቹ የተረከባትን አገር ማሻገር ይጠበቅበታል

ወጣቱ አንድነቱን አስጠብቆ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን አከርካሪ በመስበር ከአባቶቹ የተረከባትን ሉዓላዊት አገር ማሻገር ይጠበቅበታል ሲል የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አስገነዘበ።

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 400 ወጣቶች "ሁላችንም ለኢትዮጵያ ወታደሮች ነን፤ አንድም በግንባር አንድም በደጀን ለሀገሬ ዘብ እቆማለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከል መክረዋል።

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተካሄደውን ምክክር የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ነው ያዘጋጀው።

የሊጉ ፕሬዚደንት አክሊሉ ታደሰ፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያ አንድነቷን እንዳታስቀጥል ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ድብቅ አጀንዳ በመቅበር ዜጎች እንዲጠራጠሩ ማድረጉን ገልጿል።

የሽብር ቡድኑ ባለፉት 30 ዓመታት የልዩነት ትርክት እንዲንሰራፋ በማድረግ አገር ጠልነት እንዲጎለብት አድርጓል ነው ያለው።

አገር በመዝረፍ የራሱን የኢኮኖሚ የበላይነት ገንብቶ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲነሳ ሊያግዘው የሚችል ኃይል ሲያደራጅ መቆየቱንም አውስቷል።

በኢትዮጵያ ላይ እየሆኑ ያሉት የውስጥና የውጭ ጫናዎችም የሽብር ቡድኑ ባለፉት ዓመታት አገር ሲያስተዳድር የተበተበው ሴራ ውጤቶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ቡድኑ አሁንም በተከፋይ ተላላኪዎቹ አማካኝነት የኢትዮጵያ አንድነት እንዳይፀና ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ምዕራባዊያኑም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩት ተላላኪና ታዛዥ መንግስት እንዲኖር በመሻት ነውም ብለዋል።

በአገር ሉአላዊነት ጉዳይ የማይደራደር መንግስት መፈጠሩንና ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሁሉን አቀፍ ልማት በማስተሳሰር እየሄደችበት ያለውን የመልማት ስራ ለማኮላሸት እየጣሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ይህን ለመመከት በአንድነት ጸንተው መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ወጣቶችም እውነታውን ክደው ለጥቅማቸው ብቻ የሚጮሁ የመገናኛ ብዙኃንን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመመከት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሽብር ቡድኑን የጥፋት ዓላማ በቅጡ ተረድቶ አከርካሪውን በአጠረ ጊዜ በመስበር ወጣቱ ከአባቶቹ የተረከባትን አገር ማሻገር የሚጠበቅበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኝም አስገነዝበዋል።

ለአካበቢው ሠላምና መረጋጋት ዘብ መቆም እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።

ለኢዜአ ሃሳባቸውን የሰጡ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶችም አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ ለኢትዮጵያ ሠላምና ደህንነት እንደሚተጉ ገልጸዋል።

ወጣቶች በቀደምት አባቶች ደምና አጥንት የተገነባችን አገር ለማፍረስ የመጣን የሽብር ቡድን በአንድነት በመመከት ለቀጣዩ ትውልድ እንደሚያሻግሩም ተናግረዋል።

የጥፋት ቡድኑን ዓላማ ለማክሰም ተጋድሎ እደረገ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊትም ደጀንነታችንን በተግባር እናሳያለን ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆን ቡድኑ በአጭር ጊዜ እንዲጠፋ የወጣቶች ሚና ጉልህ ነው ብለዋል።

ይህም ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ሕዝቦቿ በሠላም የሚኖሩባትን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ወጣቶች ግንባር ቀደም ተሰላፊ እንደሚሆኑም አረጋግጠዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ለማጽዳት በሚደረገው ዘመቻ ከአገሪቷ አራቱም ማዕዘናት ሕዝቡ ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት የደጀንነት ድጋፉን በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም