ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች የህወሓትን የሽብር ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ተሰልፈው ይፋለማሉ

ነሀሴ 12/2013 (ኢዜአ) አገር ለማፍረስ ወጥኖ እየተንቀሳቀሰ ያለውን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ሆነው እንደሚፋለሙ ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተውጣጡ ሴቶች ገለፁ።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ 500 የሚጠጉ ሴቶች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ ኦሮሞ ባሕል ማዕከል ውይይት አካሂደዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የውይይቱ ተሳታፊዎች አሸባሪው የህወሓት ቡድን 'እኔ ያልመራኋት አገር ትፍረስ' በሚል የያዘውን አገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ እንፋለማለን ብለዋል።

የአማራ ክልል ሴቶችን የወከሉት ወይዘሮ ዕሌኒ አባይ የሽብር ቡድኑ 'ከአማራ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ' በማለት ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎ እየሰራ ነው ሲሉ አንስተዋል።

ጦርነቱ የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የህልውና ጦርነት በመሆኑ ይህን ሀገር የመበተን ሴራ ለመመከት  ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እናቶች በህልውና ትግሉ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ልጆቻቸውን "ሂድ ሀገርህን አድን ብለው መሸኘት" አለባቸውም ብለዋል።

ከአፋር ክልል የመጡት ወይዘሮ ፋጡማ አይተሌ በበኩላቸው ክልሉ ቡድኑ ጥቃት  ከከፈተባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑንና በርካታ ሠብዓዊ በደሎችን መፈጸሙአንስተው፣ ከ240 በላይ ንጹሃንን መጨፍጨፉ የማይረሳ ግፍ ፈጽሟል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትቀጥል በየቦታው ሽብር የሚነዛውን የህወሓት ቡድን የአፋር ሴቶች ከመከላከያና ከልዩ ሃይሉ ጋር ተሰልፈው እየተፋለሙት ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሴቶች ከአፋር ሴቶችና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም በጋራ መታገል አለባቸው ነው ያሉት።

ከኦሮሚያ፣ ከደቡብና ከጋምቤላ ክልሎች የተወከሉ ሴቶች በበኩላቸው የሽብር ቡድኑን ለመመከት የኢትዮጵያ ሴቶች በአንድ ድምጽ መቆማቸውን ገልጸዋል።

'ኢትዮጵያ በታሪኳ ጠላቶቿን ድል የምታደርግ እንጂ እጅ ሰጥታ የምትንበረከክ አገር አይደለችም' በማለት ምዕራባዊያን እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነት ተቃውመዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣን ኃይል ቁጭ ብለው እንደማይመለከቱ የገለጹት ሴቶቹ የኢትዮጵያ ምሁራንና ወጣት ሴቶች በሁሉም ረገድ ትግሉን ሊቀላቀሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም