ቀጥታ፡

በግንባር ለሚገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ለክልሎች ልዩ ኃይል የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ድሬዳዋ ነሀሴ 12/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ የተዋቀረው ድጋፍ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ በግንባር ለሚገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ለክልሎች ልዩ ኃይል የቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምስራቅ ዕዝ ደረጃ-3 ሪፈራል ሆስፒታል ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ዘውዴ ተረክበዋል። 

ድጋፉን ዛሬ ለመከላከያ ሠራዊት ያስረከቡት የድሬዳዋ የድጋፍ አሰባሳቢ አብይ ኪሚቴ ሰብሳቢና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ናቸው። 

በእዚህ ወቅትም አቶ ከድር በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ አገር እንድታሸንፍ በየመስኩ የሚያደርውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

በአስተዳደሩ ከልጅ እስከ አዋቂ ደም በመስጠት፤ እናትና አባቶችም ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የገለጹት።

በዛሬ እለትም ኮሚቴው ከህብረተሰቡ ያሰባሰበውን 300 ፍራሾችና 300 ጥንድ አንሶላዎችን ለሠራዊቱ ማስረከቡን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡ ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በርክክቡ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

ባለሃብቶች በአይነትና በገንዘብ ለሠራዊቱ ያደረጉት ድጋፍ በነገው እለት ርክክብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

ድጋፉን በመከላከያ ሚኒስቴር የምስራቅ ዕዝ የደረጃ-3 ሪፈራል ሆስፒታል ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ዘውዴና ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች ተረክበዋል፡፡

ኮሎኔል ብርሃኑ በዚህ ወቅት በየደረጃው የሚገኘው የድሬዳዋ ህብረተሰብና አስተዳደሩ ለሠራዊቱ እያደረጉ ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግንባር የተሰለፈው ሠራዊት አገርን የማዳን ተግባርና ኃላፊነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ በታላቅ ጀብዱ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

“በመላው አገሪቱ ለሠራዊቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ሠራዊቱ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶችን በመደምሰስ አገርን የመጠበቅና ሉአላዊነቷን የማስከበር ታሪካዊኃላፊነቱን ከምንግዜውም በላይ በብቃት እንዲወጣ ያግዘዋል” ብለዋል።

ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ሥነ-ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላትና የድጋፍ አሰባሰቢ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም