ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና ለሌሎች የጸጥታ አካላት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 12/ 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ግንባር ላይ ለሚያካሂዱት የህልውና ዘመቻ የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞች ገለጹ።

ሰራተኞቹ በግንባር እየተዋደቀ ላለው ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል።  

የመከላከያ ሰራዊት አሸባሪው ህወሃት አገሪቷን ለመበተን የወጠነውን ሴራ ለማክሸፍ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ነው።   

የህልውና ዘመቻው ፍሬ እንዲያፈራ መላው ህዝብ በገንዘብ፣ በዓይነትና በሞራል የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞችም የመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ አካላትን ለመደገፍ የቀረበውን አገራዊ ጥሪ መሰረት በማድረግ በሙያቸው ከሚሰጡት አገልግሎት ባሻገር በተለያዩ መልኮች ድጋፎችን እያደረጉ ነው።  

የተቋሙ ሰራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን የለገሱ ሲሆን፤ በወቅቱ በገቡት ቃል መሰረትም ዛሬ የደም ልገሳ አድርገዋል። 

የተቋሙ የአረብኛ ቋንቋ ክፍል አዘጋጅ አፈወርቅ ዮሃንስ እንዳለው የቀደሙት አባቶች ዋጋ ከፍለው ያቆዩዋትን አገር ለቀጣዩ ትውልድ ህልውናዋን አስጠብቆ ማስረከብ የእኛ ግዴታ ነው።

"ኢትዮጵያዊያን በአገር ጉዳይ አንደራደርም" ያለው አፈወርቅ፤ ደም ከመለገስ ባለፈ መስዋዕትነትን ለመክፈል ቆርጦ መነሳቱን ተናግሯል።

የተቋሙ ቢዝነስ ልማትና ኮርፖሬት ብራንዲንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ባዬ በበኩላቸው፤ የተቋሙ ሰራተኞች ከሳምንት በፊት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመከላከያ ሰራዊት በድጋፍ መስጠታቸውን አስታውሰው፤ "በወቅቱ ደም ለመለገስ የተገባውን ቃል ዛሬ በተግባር አረጋግጠናል" ብለዋል።      

በአሁኑ ወቅት ወጣቱን ጨምሮ አቅም ያለው በአውደ ውጊያው ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ መስዋዕነት እየከፈለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሀብት ያለው የሰራዊቱ ግዳጅ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገው ድጋፉ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

ሌላው የተቋሙ ሰራተኛ አቶ አዘነ በሱፍቃድ ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ደም በመለገሳቸው ደስተኛ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም