የግል መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን ሲሰሩ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ማድረግ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የግል መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን ሲሰሩ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ማድረግ አለባቸው
ነሀሴ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) የግል መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን ሲሰሩ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል አድርገው መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስጣኑ ከግል መገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎች ጋር በሃገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ምክክር አድርጓል ፡፡
በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ሁሉም የግል መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎቻቸውን ሲሰሩ ብሔራዊ ጥቅምን እና የሃገር ሉዓላዊነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
እንደ ሃገር ያልተረጋጋ ሁኔታ እንደመሆናችን መጠን ያልተጣሩና ምንጫቸው ያልታቁ መረጃዎችን ከማሰራጨት ይልቅ ከመዘገባቸው በፊት ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም የምዕራባዊያንን ሴራ ሊያከሽፍ ይገባል ያሉት ደግሞ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ ታደሰ ናቸው፡፡
ብርጋዴር ጀነራሉ ምዕራባዊያን በሌሎች ሃገራት ያደረጉትን እኩይ ተግባር ኢትዮጵያ አትፈቅድም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሉዓላዊነቷን እና ክብሯን አስጠብቃ የቆየች ሃገር መሆኗን ገልጸው፤ የአሁኑ ትውልድም የአባቶችን አርአያ በመከተል ለሀገሩ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ከሃገር ጥቅም አኳያ ዘገባዎችን በመስራት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በተለይ የግሉ መገናኛ ብዙሃን ግጭትን በተመለከተ ዘገባዎችን ሲሰሩ ከትክክለኛ ምንጭ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የብዙሃን መገናኛ የስራ ሃላፊዎች ስለመድረኩ አስፈላጊነት በመግለጽ ለቀጣይ ስራም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ትክክለኛ መረጃዎችን ከትክክለኛው አካል ለማግኝት አስቸጋሪ ሁኔታ ስለመኖሩ አንስተዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው እየተፈጠሩ ያሉ የመረጃ እጥረቶችን ለመፍታት ዜና አገልግሎት የበኩሉን እንደሚወጣ ገለጸዋል፡፡