ቀጥታ፡

የምእራባውያን ጣልቃ ገብነትና መዘዙ

ገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)

ሰሞኑን የአለምን ቀልብ ከያዙት ጉዳዮች መካከል አንዱ ለ20 አመታት በአፍጋኒስታን የቆየው የአሜሪካ ጦር ጠቅልሎ መውጣቱን ተከትሎ በአፍጋኒስታን የተፈጠረው ክስተት ነው።

አሜሪካ እ.አ.አ መስከረም 11 ቀን 2001 ላይ ከተፈጸመባት የሽብር ጥቃት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ኦሳማ ቢን ላደን እና አል-ቃይዳን ይደግፋል ያለችውን ታሊባንን ከስልጣን ለማውረድ በእ.አ.አ 2001  ነበር አፍጋኒስታንን የወረረችው።

አሜሪካ ጦሯን ወደ አፍጋኒስታን ካሰገባች በኋላ ታሊባንን ለመዋጋት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ስታፈስ መቆየቷን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን ከ970 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓን የብራውን ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያመለክታል። የወታደሩ ቁጥርም በአንድ ወቅት ከ110,000 በላይ ደርሶ እንደነበር ይነገራል።

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአፍጋኒስታን የተደረገው ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ የጠፋው የሰው ህይወት በቀላል የሚገመት አይደለም። የብራውን ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ2019 በሰጠው መረጃ መሰረት ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 2001 ጀምሮ በአፍጋኒስታን በብሔራዊ ጦር እና ፖሊስ የጠፋው ሕይወት ከ64 ሺህ በላይ እንደሚሆን ተገምቷል። አሶሼትድ ፕሬስ ባወጣው መረጃ መሰረት በጦርነቱ ከ47 ሺህ በላይ አፍጋናውያን ንጹሐን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከ400 በላይ የእርዳታ ሰራተኞች ሲገደሉ 72 ጋዜጠኞች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃው ያመለክታል። ይህ ሁሉ ሀብት ከወደመና ህይወት ከቀጠፈ በኋላ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለቅቃ ስትወጣ የተፈጠረው ምስቅልቅል የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል። አሜሪካ በአፍጋኒስታን ከቆየችበት ረጅም ጊዜ አኳያ በሀገሪቱ የተፈጠረው ክስተት ምን ያህል ሃላፊነት የጎደለው ስለመሆኑ ለዓለም ያሳየ ሆኗል።  

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው በአፍጋኒስታን የነበራት ተልእኮ የሀገር ግንባታ እንዳልነበረ ተናግረዋል። በዚሁ ንግግራቸው "አንድም የአሜሪካ ወታደር በአፍጋኒስታን መዋጋትም ሆነ መሞት የለበትም፣ አፍጋኒስታን ወታደሮች ለማይዋጉለትና ለማይሞቱለት ጦርነት ለምን ሲባል አሜሪካዊ ወታደር ተዋግቶ ይሞታል?" ሲሉ ነበር በጥያቄ መልክ የገለጹት። የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣቱን ተከትሎ በተፈጠረው ክስተት የጆ ባይደን አስተዳደር ክፉኛ ተተችቷል።

በአፍጋን ዋና ከተማ ካቡል አየር ማረፊያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሀገሪቱን ለመልቀቅ ሲያደርጉት በነበረው ትንቅንቅ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን ጎማ ላይ እስከመንጠልጠል ደርሰው ታይተዋል፡፡ በዚህም በርካታ ሰዎች አውሮፕላኑ ሲያኮበኩብ እና ከተነሳ በኋላ ወድቀው የሞቱ መኖራቸውንም የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።    

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ (ትንሹ) ጦራቸውን ወደ አፍጋኒስታን ሲልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአሸባሪው አልቃይዳ መጠለያ የሰጠውን ታሊባንን መደምሰስ እና አፍጋኒስታንን ከዴሞክራሲ ጋር ማስተዋወቅ የሚል ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ አዋጭ እንዳልሆነ በርካቶች ቢወተውቱም ድምጻቸውን የሚሰማ አላገኙም።

እንዲያውም ከአፍጋኒስታን በተጨማሪ ጦራቸውን ወደ ኢራቅ በመላከ የሳዳም ሁሴንን አስተዳደር ከስልጣን ለማስወገድ ከፍተኛ ዘመቻ አድርገው እንደነበር የሚታወስ ነው። በሁለቱም ሃገራት ውስጥ በተደረጉ ጦርነቶች ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ ከመፈጠሩም ባሻገር በርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ብዙዎች ተፈናቅለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ሀገር ጥለው ተሰደዋል። በተመሳሳይ የዚህ ዓይነቱ ክስተት በሊቢያ፣ በሶሪያ፣ በየመን እና በሌሎችም ሀገራት ተከስቷል።

አሜሪካ አጋሮቿን በመያዝ ከወረራ ባልተናነሰ መልኩ ጣልቃ በገባችባቸው ሀገራት ሁሉ አሳክታዋለች ተብሎ የሚነገርላት ነገር ቢኖር የሀገራቱን መሪዎች ከስልጣን እንዲወገዱ ወይም ለእነርሱ የሚመች ደካማ አስተዳደር ያለው መንግስት መፍጠር ነው። በአሜሪካ ጣልቃገብነት ምክንያት በርካታ ሀገራት ያለ መሪና ምልክት ስለመቅረታቸው ሊቢያና ኢራቅ ጉልህ ምሳሌዎች ናቸው። የአፍጋኒስታን የ20 ዓመታት ቆይታም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

በኢንተርናሽናል ሴኩሪቲ ፕሮግራም ውስጥ በተመራማሪነት ሲያገለግሉ የነበሩት አላን ኩፐርማን “Lessons from Libya: How Not to Intervene” በሚል ርእስ በፃፉት ትንታኔ ምእራባውያን የሊቢያ መሪ የነበሩትን ሞሐመድ ጋዳፊን ከስልጣን ለማስወገድ የተሳሳተ ጣልቃ ገብ አቅጣጫ መከተላቸውን ገልጸዋል። ምእራባውያን በሊቢያ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት በዴሞክራሲ ሽፋን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ለማስወገድ እንጂ ለዜጎች ታስቦ አለመሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል። አሜሪካ የምታደርጋቸው ሁሉን አቀፍ የጣልቃገብነት ሙከራዎችና ትግበራዎች ያልተሳኩና ተቃራኒ ውጤቶችን ያስከተሉ ስለመሆናቸው በዝርዝር አብራርተዋል።

ምእራባውያን በሊቢያ ጣልቃ ገብተው ጦር የመዘዙት ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለማሰፈን የሚል ቢሆንም የተፈጠረው ግን የዚህ ተቃራኒ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። በሊቢያ የተፈጠረው ክስተት ቢኖር የተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነት መጨመር፣ ሽብርተሽነት ማንሰራራት እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት  መባባስ፣ አስከፊ ድህነት መንሰራፋት ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የዚህ ዓየነቱ ክስተት ለምእራባውያን ውድቀት መሆኑን በመግለጽ ትምህርት ሊወስዱበት እንደሚገባ ብዙዎች አጽንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም