የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከወሰደው ብድር 50 በመቶ እዳ ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞር ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከወሰደው ብድር 50 በመቶ እዳ ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞር ተደረገ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወሰደው ብድር ውስጥ 191 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር (50 በመቶ) እዳ ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞር ተወሰነ።
መንግሥት ከፍተኛ እዳ ያለባቸው የልማት ድርጅቶች እዳ እንዲሰረዝና ወደ ካፒታል እንዲዞር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው ዕዳው የተሰረዘው ተብሏል።
በዚህም ተቋሙ ከወሰደው ብድር 50 በመቶ (191 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር) እዳ ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞርለት መደረጉን ተቋሙ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ያስታወቀው።
ውሳኔው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ዕዳና ኃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዛሬ ባደረጉት የጋራ ሥምምነት የተላለፈ መሆኑን ተገልጿል።
በሥምምነት መሰረት ተቋሙ እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2016 ከንግድ ባንክ የወሰደው ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በ2017 የወሰደው ብድር በከፊል ወደ ካፒታል እንዲዞርለት ነው ውሳኔ የተላለፈው።
የዕዳ ስረዛው ብድሩን ከነወለዱ የሚያስቀር ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት 17 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በቀጣይ በጀት ዓመት 18 ነጥብ 81 ቢሊዮን ብር ወለድ ከመክፈል ታድጎታል።
ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት መክፈል የነበረበትን 17 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ወለድ የተቋሙን የ2013 በጀት ዓመት ገቢ ከ85 በመቶ በላይ የሚሸፍን ነው ተብሏል።
በሥምምነቱ መሠረት ባንኩ ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የሰጠው ብድር ወደ ካፒታል በመዞሩ 191 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብሩን የሚጠይቀው ከተቋሙ ሳይሆን አዲስ ከተቋቋመው የመንግሥት እዳና ኃብት ኮርፖሬሽን ላይ ይሆናል ተብሏል።
ያም ሆኖ ተቋሙ እ.ኤ.አ. ከ2017 ወዲህ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዳቸውን ቀሪ ብድሮች ግን በራሱ የሚከፍል እንደሆነ ነው በመግለጫው የተጠቆመው።
የእዳ ስረዛው ተቋሙ የነበረበትን እዳ ወደ ካፒታል ስለሚያዞረው ተቋሙን የሒሳብ መዝገቡን በማስተካከል ወደ ጤነኛነት ደረጃ እንደሚመልሰውም ተጠቁሟል።
በተጓዳኝም እዳ ስረዛው ተቋሙን ጠንካራና ተወዳዳሪ በማድረግ ወደፊት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አቅም እንደሚፈጠርለት በመግለጫው ተመላክቷል።
ተቋሙ ባለፉት ሦስት አመታት ባደረገው ኦዲት ከትትል ነጻና የፋይናስ ሥርዓቱም ጤነኛ እየሆነ መምጣቱ ተጠቁሟል።
በዚህም የተቋሙ አጠቃላይ ገቢ 13 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተመልክቷል።
ከፍተኛ እዳ ካለባቸው የልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል፤ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪና የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እዳ እንዲሰረዝላቸው ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።