ቀጥታ፡

ተላላኪ ለተላላኪ መቀጠር አይችልምና ተላላኪው ሸኔ ከሀገር አፍራሹ ህወሃት ጋር ያደረገውን ጋብቻ ማፍረስ ይገባል

ነሐሴ 12/2013 (ኢዜአ) ተላላኪ ለተላላኪ መቀጠር አይችልምና ተላላኪው ሸኔ ከሀገር አፍራሹ ህወሃት ጋር ያደረገውን ጋብቻ ማፍረስ ይገባል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

የለገጣፎ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሃት ያደረጉትን ሀገር የማፍረስ ስምምነት የሚቃወምና  ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት የሚገልጽ  ሰልፍ አካሄደዋል።

በፈረሰኛ ታጅበው አደባባይ የወጡት ነዋሪዎቹ ፤ ባዳና ባንዳን በአንድነት እንመክታለን፣  አሸባሪው ህወሃትና ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው፣ ሸኔ ኦሮምኛ ተናጋሪ ህወሃት ነው የሚሉት መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

በሰልፉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንዳሉት፤ ተላላኪ ለተላላኪ መቀጠር አይችልምና ተላላኪው ሸኔ ከሀገር አፍራሹ ህወሃት ጋር ያደረገው ጋብቻን ማፍረስ አለበት።

አሸባሪው ሸኔ ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ያደረገውን የሰይጣን ጋብቻ ማፍረስ አለበት በማለትም ጠቅሰዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ  የእኩልነት ጥያቄ ነው ያሉት ሃላፊው፤ ላለፉት 27 ዓመታት ጥፍር ሲነቅልና የሰውን ልጅ ዝቅ አድርጎ መግዛትን የለመደውን ህወሃት በአቋራጭ ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ የተደረገው ጋብቻ አይሳካም ብለዋል።

የውጭ ሃይሎችም  በስንዴ ስም የተቀበረውን የአሸባሪው ህውሃት ቡድን አቧራ አራግፋችሁ ወደ ስልጣን ለመመለስ የምታደርጉት ድርጊት ጦረኝነት ነውና እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ  አንሱ" ሲሉ ዶክተር ቢቂላ ያስታወቁት።

ዛሬ ከአሸባሪው ጋር ውል የገቡት ተላላኪዎቹ የኦሮሞ ህዝብ ጥፍር ሲነቀል በነበረበት በዚያ ጨለማ ወቅት ያልተከላከሉለት ባንዳዎች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ናቸው።

ወስነው መከላከያን እንደተቀላቀሉት ወጣቶቻችን ዛሬ ላይም በምክንያት መወሰን የሚችሉ ወጣቶቻችን የማንም ተላላኪ መሆን አይችሉም ብለዋል ከንቲባዋ።

ነዋሪዎቹ  በበኩላቸው፤ ተላላኪው ሸኔና ህውሃት የደረጉትን ሀገር የማፍረስ ስምምነት ለመቃወምና  ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አጋርነታቸውን ለማሳየት ሰልፍ እንደወጡ ተናግረዋል።

ወጣት አብዲ ረፌራ በሰጠው አስተያየት፤  ህወሃትና ሸኔን መቃወም ብቻ ሳይሆን ወደ ጉድጓድ እንመልሳቸዋለን ብሏል።

አቶ ጌትነት ሃይልዬም ገዳዩን ህወሃትና ሸኔን አምርረን እንቃወማለን ይላሉ።

በተለይም እንደ ሴትነቴና እናትነቴ እናቶችን የሚያስለቅሰውን ህወሃትና ሸኔን እቃወማለሁ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሃብታም ዳምጤ ናቸው።

የለገጣፎ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጥፋተኞቹን ህወሃትና ሸኔን ከመቃወም ባለፈ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር  እስከ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም በጋራ በገቡት ቃል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም