የኢትዮጵያዊያን አይነተኛ ባሕሪይ በችግር ጊዜ መሰባሰብና በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያዊያን አይነተኛ ባሕሪይ በችግር ጊዜ መሰባሰብና በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ነው
ነሐሴ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን አገር የገጠማትን የሕልውና አደጋ በድል እንድትወጣ በታሪክ የሚዘከረውን በአንድነት የመቆም እሴት መድገም እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ።
ኢትዮጵያ በዘመኗ በርካታ አደጋዎች እንዳጋጠማት የሚጠቅሱት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳግማዊ ተስፋዬ፤ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ አደጋ የደቀነው አሸባሪው ህወሓት ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ እንደነበረው ለአዜአ ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት መንግስት መስርቶ ካስተዳደረ በኋላ እውነተኛ ባህሪው መውጣቱን ገልጸዋል።
"ቡድኑ የኢትዮጵያ ጠላት የሆኑ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን የሕልውና አደጋ መፍጠሩ ትክክለኛ ማንነቱን ማሳያ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም" ሲሉ ገልጸውታል።
"ኢትዮጵያ በገጠሟት አደጋዎች ትበታተናለች እየተባለ ተነግሮ ነበር" ያሉት ዶክተር ዳግማዊ፤ "ይሁንና በችግር ጊዜ እንደ አለት በሚጠነክሩና በአንድነት አጥር በሚሰባሰቡ ብርቱ ልጆቿ ሁሉንም በድል አልፋዋለች" ብለዋል።
ዶክተር ዳግማዊ ኢትዮጵያዊያን አሁንም በችግር ጊዜ የመሰባሰብና ጠላት ላይ የማያዳግም ርምጃ የመውሰድ ባሕላቸውን በአሸባሪው ህወሓት ላይ መድገም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
'የኢትዮጵያ ጠንካራና ለማንም የማትገዛ ሉዓላዊት አገር መሆን በምዕራባዊያን ዘንድ አልተወደደም' ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ ናቸው።
"የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት መዳፈር የሚሹ አካላት እንደ ህወሓትና ሸኔ ያሉ የውስጥ ተላላኪዎችን በወኪልነት ያስቀምጣሉም" ብለዋል።
በመሆኑም በሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ የመንና ሌሎች አገራት የሰሩትን አገር የማፈራረስ ሴራ በኢትዮጵያ ለመድገም የሚቋምጡ የውጭ አካላትን ለመመከት ሁሉም በአንድነት መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያዊያን ምዕራባዊያን አገር ለማፍረስ የሚጠቀሙባቸውን የውስጥ ባንዳዎች በመመከት የታሪክ አደራቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ጠላት ሀሰቱን እውነት በማስመሰል ዓለም አቀፉን ማኀበረሰብ እያሳሳተ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የተማረው ማኅበረሰብ የዲጂታል ሠራዊት በመሆን የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻውን መቀልበስ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ውጤቶችም አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የተረዱና ችግር መፍታት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።