ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያሴሩትን አሸባሪዎቹን ሕወሃትና ሸኔ እንታገላለን

አዲስ አበባ ነሐሴ 12/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያሴሩትን አሸባሪዎቹን ሕወሃትና ሸኔ እንዲሁም ከውጭ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመቀልበስ ለሚደረገው የህልውና ትግል እስከ መስዋዕትነት ድረስ እንደሚደግፉ የቡራዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በቡራዩ ከተማ ተካሂዷል።

አሸባሪዎቹ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረሰ የሚያደርጉትን የሽብር ተግባር ለመቀልበስ ዝግጁ መሆናቸውን የሠልፉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች አሸባሪዎቹን ሕወሃትና ሸኔን ለመደምሰስ የሚደረጉትን ትግል በተለያዩ መንገዶች እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ከሰልፈኞቹ መካከል ወጣት ተሊላ መገርሳ እንደገለጸው፤ ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች አገርን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ሴራ ለማምከን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል።

አገር አፍራሾቹን ለሚዋጋው ለአገር መከላከያ ሠራዊትም የጥሬ ገንዘብ ከመስጠት ጀምሮ የሚችለውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገረው።

ከሠራዊቱ ጋር በመቀላቀል እነዚህን የሽብር ቡድኖቹን ለመደምሰስ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱንም ወጣት ተሊላ አስረድቷል።

"ሸኔ የሽብር አጋሩ ከሆነው ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ሆኖ ለኦሮሞ ህዝብ መብት እታገላለሁ በማለት እኛን ማታለል አይችልም፤ ሁለቱም ጠላቶቻችን ናቸው፤ ስለዚህም በአንድነት እናጠፋቸዋለን" ብለዋል።

ሌላው በሰልፉ የተሳተፈው ወጣት አብዲሳ በቀለ በበኩሉ እንደገለጸው፤ አሸባሪው ህወሓትና ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው።  

እነዚህንም ቡድኖችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት "ከአገር መከላከያ ሠራዊትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ባለኝ አቅም ሁሉ እሰለፋለሁ" ብሏል።

የሽብር ቡድኖቹ አሁን ላይ በሐሰተኛ መረጃ ሕዝቡን ከማሸበር ውጭ ምንም አቅም እንደሌላቸው ገልጾ፤ "የቡድኖቹን ሴራ አሁኑኑ መክሸፍ ይገባዋል" ነው ያለው።  

ወይዘሮ ዘውዲቱ ዳዲ በበኩሏ አሸባሪ የህወሓት ቡድን ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲዘርፍና ሲገድል መቆየቱን አስታውሰዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አሸባሪዎቹን ሕወሃትንና ሸኔን ለመደምሰስ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

"የአሸባሪው ህወሓትን ለመቅበርና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ እኔም የበኩሌን እወጣለው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አረገወይን አራጌ ናቸው።

ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት ሆነን "የአገራችን አንድነት ለማስቀጠል መሥራት ይኖርብናል" ብለዋል።

አሸባሪው ሸኔና ሕወሓት ጥምረታቸውን መግለጻቸው "አዲስ ነገር አይደለም" ያሉት ደግሞ የቡራዩ ከተማ ከንቲባ አቶ ጀግናው ግዛው ናቸው።

"አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ውስጥ የማይረሳ ጥቁር አሻራ ያሳረፈ ድርጅት ነው" ያሉት ከንቲባው፤ ሕዝቡ ያገኘውን ድል ለመቀልበስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ጋር የሽብር ሥራውን እንደቀጠለበት ተናግረዋል።

አሸባሪው ሸኔ ለግል ጥቅሙ ሲል የኦሮሞን ህዝብ ሲገድል ከኖረው አሸባሪው ህወሓት ጋር ጥምረት መፍጠሩ "ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ንቀት ያሳያልም"ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ለአገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረው፤ ወጣቱ ደግሞ እንደጀመረው የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል።

ህብረተሰቡ የሽብር ቡድኖቹን ለማጥፋት ከሚደረገው ሥራ በተጨማሪ አካባቢውን ሰላም እንደጀመረው ሊጠብቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሰልፈኞቹ "ሸኔ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወያኔ ነው!"፣ "አገራችን ለማዳን መስዕዋትነት እንከፍላለን"፣ "አገራችን በአሸባሪዎች አትፈርስም" "እኛ የኦሮሞ ቄሮና ቀሬ የሸኔና የወያኔ ጋብቻ በጽኑ እናወግዛለን"--የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም