ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና አገር የማዳን ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ነሃሴ 12/2013(ኢዜአ)  መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በማስከበርና አገር በማዳን ዘመቻው ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና የመከላከያ ወታደራዊ መኮንኖች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው።

የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ ኢትዮጵያ የገጠማትን የሕልውና ፈተና ለመወጣት መገናኛ ብዙሃን ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ35 በላይ የውጭ ሚዲያዎች እንዳሉ ጠቅሰው በተለይም በትግራይ በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ከተፈፀመ በኃላ ከ100 በላይ የውጭ ጋዜጠኞች ፈቃድ አግኝተው ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ገልፀዋል።

ዳሩ ግን የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ያላካተቱና ለሽብር ቡድኑ የወገኑ ዘገባዎችን በመዘገብ ኢትዮጵያ ላይ መዝመታቸውን አንስተዋል። 

በአንፃሩ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ሕልውና ለመጠበቅ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረጉ ባሉበት የአገር ውስጥ የንግድ መገናኛ ብዙሃን ወጣ ገባ ስራዎችን ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

ዳይሬክተሩ መገናኛ ብዙሃኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ወገንተኛ ሆነው ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማድረስ እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት። 

በውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር የኢጋድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በተለይም ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ ሊቆጣጠሯት የሚሹ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን አንስተዋል።

የምዕራባዊያኑ የወቅቱ የፀረ ኢትዮጵያ ዘመቻም አገሪቷን በመበታተን ጂኦ ፖለቲካውን መቆጣጠር መሆኑን ገልፀው ለዚህ ደግሞ የጎረቤት አገራትና የህወሓት መሰል ሽብርተኞችን በመጠቀም ከጀርባ እየወጓት ነው ብለዋል።

በመሆኑም በየዘመናቱ በርካታ ፈተናዎችን የተሻገረችው ኢትዮጵያ የገጠማትን የወቅቱን ፈተና እንድትወጣ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። 

የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን በራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት የተቃኘ መሆኑን ገልፀው ወቅቱ የአገር ውስጥ ሚዲያውን አገር ለማዳን በትጋትና በትብብር መስራት የሚጠይቅበት መሆኑን ተናግረዋል። 

የመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ወቅቱ የመከላከያ ሠራዊትን ዐውደ ውጊያ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በየሙያቸው የሚያደርጉትንም ትግል ይፈልጋል ብለዋል። 

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መገናኛ ብዙሃን እንደ ባለድርሻ ዘርፍ በውጭ ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚነዛውን የፀረ ኢትዮጵያ አቋም መከላከል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። 

መገናኛ ብዙሃን በዐውደ ውጊያ በመገኘት ተጨባጭ መረጃ የማድረስ፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥና ሠራዊቱን በሙያቸው መደገፍ እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት። 

'የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ኢትዮጵያ ታሸንፋለች' ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ ለዚህ ግን መገናኛ ብዙሃን ዋናውን አገር የማዳን ተልዕኮ ማዕከል አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም