ህዝቡ የአሸባሪው ህወሃት የስነልቦና ጦርነት ሰለባ መሆን የለበትም -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ የአሸባሪው ህወሃት የስነልቦና ጦርነት ሰለባ መሆን የለበትም -ምሁራን
አርባ ምንጭ ነሐሴ 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ የአሸባሪው ህወሀት የስነ-ልቦና ጦርነት ሰለባ መሆን የለበትም ሲሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ምሁራን አስገነዘቡ፡፡
ኢዜአ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ምሁራን አሸባሪው ህወሀት ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ግርማ ጉራ እንዳሉት እስካሁን በተደረገው ጦርነት አንድም ድል ያልተቀዳጀው ህወሀት የሀሰት ድል ደጋግሞ በማውራት በህዝቡ ስነ-ልቦና ላይ ጫና ለመፍጠር እየዳከረ ነው።
"አሸባሪው ቡድን 'ትግራይ መፈንጫቸው ሳይሆን መቀበሪያቸው ትሆናለች' በሚል በተደጋጋሚ ፎክሮ የኋላ ኋላ እንደ አይጥ ጉድጉድ መግባቱ ትልቅ ማሳያ ነው" ብለዋል።
ቡድኑ ዛሬም ድል እንደቀዳጀ በማስመሰል የሚነዛው የሀሰት ወሬ ህዝቡን እያደናገረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ሙሉ እምነት በመጣል ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎችን መከታተል እንደሚገባው ጠቁመዋል።
"አፍሪካዊያን በቅኝ የተገዙት ነጮች ከእኛ የበላይ ናቸው በሚል ስነ-ልቦና ጫና ውስጥ በመውደቃቸው እንጂ በእርግጥ ነጮች የበላይ ስለሆኑ አይደለም" ያሉት ደግሞ ሌላው የዘርፉ ምሁር መምህር ደምሴ ተፈራናቸው ።
"ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው" እንደሚባለው አሸባሪው ህወሀት ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ህወሀት በስልጣን ዘመኑም ቢሆን መልካም ነገር አድርጎ ሳይሆን ደጋግሞ በማውራት በህዝቡ ላይ ጫና ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል።
ቡድኑ አሁንም እንደልማዱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያስመዘገበውን ድል የራሱ አድርጎ በማውራት ከንቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ህዝቡ ውሸትን በመደጋገም እውነት ለማስመሰል በሚጥረው የአሸባሪው ቡድን ወሬ ሳይሸበር እውነቱን ከትክክለኛ ምንጭ በማጣራት መረዳት እንዳለበት አሳስበዋል።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የስነ ልቦና መምህር ማርቆስ ኮንካ በበኩላቸው "ህወሀት አስቀድሞ የሀሰት መረጃ በመልቀቅ የህዝቡን ስነልቦና መቆጣጠርና ደጋፊዎቹን በማታለል ተቀባይነት ለማግኘት እየሰራ ነው "ብለዋል።
መንግስት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትኩሱ ለህዝብ በማድረስ የአሸባሪውን አላማ ማምከን እንዳለበት ጠቁመዋል።