ቀጥታ፡

የአካባቢያችንን ሰላም በማረጋገጥ የሸኔን የጥፋት ተልዕኮ በጋራ ማምከን ይጠበቅብናል

ሀዋሳ ነሐሴ 12/2013(ኢዜአ) የአካባቢያችንን ሰላም በማረጋገጥ የሸኔን የጥፋት ተልዕኮ በጋራ ማምከን ይጠበቅብናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ ።
የሲዳማ፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች የፀጥታ መዋቅሮች በሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በሀዋሳ ምክክር አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ  በወቅቱ እንደተናገሩት አሸባሪው የህወሀት ቡድን ለ27 ዓመት ህዝብን ሲጨቁንና ሲበዘብዝ ወደ ነበረበት ሥልጣኑ ዳግም ለመመለስ የሽብር ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።

ቡድኑ በሀገር ህልውና ላይ የደቀነውን ሥጋት በመመከት እየተወሰደበት ያለውን እርምጃ ለማዳከም ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ህወሀት አገር የማፍረስ አጀንዳውን ለማሳካት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላትነቱን ካረጋገጠው ሸኔ ጋር በመተባበር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥትም የሸኔን እንቅስቃሴ ለመመከት እየሰራ መሆኑንም በማመልከት።

"አጎራባች  ክልሎች አካባቢያዊ ሰላማችንን በማጠናከርና በማስጠበቅ የሸኔን የተላላኪነት ሚና ማምከን ይገባናል" ብለዋል።

የአሮሚያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ በበኩላቸው ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ትክክለኛ መሥመር ይዞ መመራት አለበት የሚሉ አመራሮችን ጭምር ሲገድልና ሲያስገድል የኖረ የሽብር ቡድን እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በህወሀት አመራሮች ዕዝ የሚንቀሳቀስ ወታደራዊ ክንፍ እንደነበረው ገልጸዋል።

"የህወሀት አገር የማፍረስ አጀንዳ የሚጠፋው ሸኔን ማጥፋት ሲቻል በመሆኑ ብሔርና አስተዳደራዊ ክልል ሳይወስን የጋራ ጠላታችንን ተባብረን ማስወገድ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በበኩላቸው ሸኔ በአጎራባች ክልሎች ከወሰን ጋር የተያያዙ ግጭቶችን በማባባስ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃትና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈጽም መቆየቱን ጠቁመዋል።

ጥቃቱን ለማስቆም ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችን በማቆየት በአገራዊ ጉዳይ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሸኔ በፀጥታ ሀይሎች ጥምረት እየተወሰደበት ካለው እርምጃ ባሻገር በከተሞች ለሽብር ተግባር ያሰማራቸው ግለሰቦችም  በቁጥጥር ሥር  እየዋሉ መሆኑን ኃላፊ አስታውቀዋል።

በመድረኩ የሲዳማ ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልል አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም