በእርዳታ ሽፋን የፖለቲካ ሴራ … - ኢዜአ አማርኛ
በእርዳታ ሽፋን የፖለቲካ ሴራ …
መንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)
የቀድሞ የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል አና ጎሜዝ በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ላይ የምእራቡ ዓለም የእርዳታ ድርጅቶች በሰብዓዊ ድጋፍ ሽፋን የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት ይንቀሳቀሳሉ በማለት ገልጸዋል። እነዚህ ድርጅቶች ፍላጎታቸው ለማሳካት በአንድ ሀገር የሚከሰት ችግር በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ እንደማይፈልጉ፤ ይልቁንም ቀውሱ እንዲራዘም የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ የምዕራቡ ዓለም የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ፖለቲካዊ ተልእኮ የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ ናቸው። ጂኦ-ፖለቲክስ ፕሬስ የተባለው የመረጃ ቋት በቅርቡ ባወጣው ትንታኔ እንዳመለከተው ለበርካታ ሀገራት መፍረስ እና ለህዝቦች መፈናቀል ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል አንዱ የተራድኦ ድርጅቶች ፍቃድ ከወሰዱበት ዓላማ ውጪ ሰብዓዊ ልማትን ሽፋን በማድረግ የሚወክሏቸውን ሀገራት ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ድብቅ ተልዕኮ ተቀብለው መሰማራታቸው እንደሆነ አስነብቧል:: በዚሁ ትንታኔ ላይ እንደተገለጸው ምእራባውያን የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች “ባስማ ፕሮጀክት” በሚል የእርዳታ ስም ሶሪያን ለማፍረስ እንደተጠቀሙበት አመልክቷል።
አና ጎሜዝ ምእራባውያን የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ ስውር የፖለቲካ አጀንዳ ያለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ። እነዚህ ድርጅቶች በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያን ራሷን ችላ ማየት አይፈልጉም ሲሉ ይገልጻሉ። ይልቁንም ላለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን በኢ-ዲሞክራሲያዊ መንገድ ሲመራ የነበረው አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ወደ ስልጣን ለማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል። በእርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ከተሰጣቸው ተልእኮ ውጪ የፖለተካ ሴራ የሚያሴሩ ስለመሆናቸው አንዱ ማሳያ በቅርቡ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሶስት የእርዳታ ድርጅቶችን ፈቃድ ማገዱን ማስታወስ በቂ ይሆናል።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) በወረቀት ላይ የሰፈረው ዋነኛ ተልዕኮው የአሜሪካን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መነሻ በማድረግ ሀገራት በሚያጋጥማቸው ችግሮችና አደጋዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ሰብዓዊ ልማት እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ከበስተጀርባው ፖለቲካዊ ሴራ የሚሰራበት ስለመሆኑ በርካታ አስረጂዎች አሉ።
የድርጅቱ ሀላፊ ሳማንታ ፓወር በቅርቡ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ያደረጉትን የስራ ጉብኝት ተከትሎ በማጠቃለያቸው ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት “በሽብርተኝነት ስለተፈረጀው የህወሃት ቡድን የአሜሪካ አቋም ምንድነው?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ እኔ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ እንጂ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ሃላፊዋ በግል የቲውተር ገጻቸው ላይ ጭምር ያሰፈሯቸው መልዕክቶች ከሰጡት ምለሻ ጋር የሚቃረን ነው።
ሳማንታ ፖወር “ህወሃት ታጣቂዎቹን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች በአስቸኳይ ያስወጣ፤ የአማራ ክልላዊ መንግስትም እንዲሁ ታጣቂዎቹን ከምዕራባዊ የትግራይ አካባቢዎች ያስወጣ፤ የኤርትራ መንግስትም እንዲሁ ጦሩን በፍጥነት እና በቋሚነት ከኢትዮጵያ እንዲያወጣ አሜሪካ ጥሪ ታደርጋለች፤” በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። ይህም የእርዳታ ድርጅቶች ምን ያህል በፖለቲካው ውስጥ በመግባት ተዋናይ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን የሃላፊዋ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ድርድር እንዲደረግ በመንግስት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር መሆኑን በስፋት መዘገባቸው በግልጽ የፖለቲካ ሴራ መያዛቸውን አሳብቆባቸዋል።
አብዛኛዎቹ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ወደ ትግራይ እርዳታ ለማድረስ መንግስት በሱዳን በኩል ያለውን ኮሪደር እንዲከፍት እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታዎች ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ማድረግ እንዳለበት ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል። ሳማንታ ፖወር ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም ይህንን ለማስፈጸም እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ድርጅቶች መንግስት እርደታ ለማሰራጨት የየብስም ይሁን የአየር በረራ አመቻችቶ እያለ በሱዳን በኩል ኮሪደር መከፈት አለበት የሚለው ለምን አስፈለገ? በማለት ብዙዎች ሞግተዋል። የሰብአዊ እርዳታዎችን ወደ ትግራይ ለማስገባት ከታሰበ ከሱዳን ይልቅ ቅርብ የሆኑ ሌሎች መስመሮች አሉ። ይህም በመሆኑ ዓላማው በእርዳታ ሽፋን ለአሸባሪው ህወሓት የጦር መሳሪያና ቁሳቁስ እንደልብ ለማስገባት ታቅዶ እንደሆነ ብዙዎች ተናግረዋል።
ምእራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ በአዎንታ አልተቀበሉትም። ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያን ለመበታተን ወይም ለማዳከም የትኛውንም ዓይነት መንገድ ከመከተል አልቦዘኑም። በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኩል የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በስፋት በማሰራጨት ተጠምደዋል። የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶቻቸው ስውር የፖለቲካ ሴራዎቻቸውን አላቋረጡም። ለዚህም በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር በየእለቱ አዳዲስ ፈጠራዎችን በማካተት ፕሮፖጋንዳቸውን አጠናክረዋል።
የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ምእራባውያን የሚፈልጉትን ለማሳካት ስውር የፖለቲካ ሴራ በመንደፍ ሀገራቱን ለማዳከም ይሰራሉ። እንደሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ ሰሞኑን ደግሞ አፍጋኒስታን ላይ የተስተዋለውም ይኸው ነው። እነዚህ ሀገራት በምእራባውያን የፖለቲካ ሴራ ወደማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፤ ተንኮታኩተውም ወድቀዋል። በእነዚህ ሀገራት የፈጸሙትን በኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር የሚያሴሩት ሴራ በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኩል ገፍተው እየቀጠሉበት ይገኛሉ። ይህንን ሴራ መቋቋም የሚቻለው ከምንም በላይ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ነው። ኢትዮጰያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ ድርድር እንደማያውቁ ታሪክ ይናገራልና አሁንም ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት አንድ ላይ መቆም ከመላው ኢትዮጵያውያን ይጠበቃል።