ቀጥታ፡

ሁሉም በአንድነት በመነሳቱ የህወሃት የሽብር ቡድን የሃገር ስጋትነት በቅርቡ ያበቃል

ደሴ  ነሃሴ 12/2013 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር በአንድነት አሸባሪውን ህወሃት ለማስወገድ በመነሳቱ የቡድኑ የሃገር ስጋትነት በቅርቡ ያበቃል ይላሉ የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል።

የሃገርን አንድነትና ሉአላዊነት ከማስቀጠል የሚቀድም ምንም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት እንደማይኖር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማው ተጠባባቂ ሃይል ምረቃ ላይ ከንቲባው እንደተናገሩት አሸባሪው የህወሓት ቡድን እያደረሰ ያለውን ጥፋት በጋራ መክተን ወደ ልማታችን ለመዞር ሁሉም የየድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

ወጣቱ ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቁም ባለፈ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ተጠባባቂ ኃይል ወጣቶች ብቁ በመሆናቸው ለዛሬ ምርቃ እንደበቁም ተናግረዋል።

ከተማዋን 24 ሰዓት ከመጠበቅ ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወደ ግንባር ዘምተው አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ በቂ ዝግጅት አድርገው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ በበኩላቸው “የአሸባሪው ህወሓትን እድሜ በማሳጠር እያደረሰ ያለውን ዘግናኝ ጥፋት ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ያለ ልዩነት በቅንጅት እየሰራን ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።

“አሸባሪው የህወሓት ቡድን የኢትጵያውያን የጋራ ጠላት በመሆኑ በትብብር በመደምሰስ ዳግም እንዳይነሳ ማድረግ ይገባል”ብለዋል።

ቡድኑ ባካሄደው ወረራ በሚደርስበት አካባቢ ሁሉ ግድያ፣ ጭፍጨፋና ዘረፋ እየፈጸመ ከመሆኑም ባለፈ ወጣቱን አፍኖ ወደ ማይታወቅ አካባቢ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

''አማራን አዳክሞ አገር ለማፍረስ የጀመረውን ሴራ በማክሸፍ የቡድኑን እድሜ በማሳጠር ቀጣይ ለህዝብ ስጋት በማይሆን መልኩ ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበርም ያለ ልዩነት በቅንጅት እየሰራን ነው'' ሲሉ ገልፀዋል።

''አገርና ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው ፖለቲካም የሚኖረው'' ያሉት ሊቀመንበሩ አገር አፍራሹን ቡድን ለመደምሰስ ከመንግስትና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ አንድ ሆነን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የአሸባሪው ቡድን ሃገር የማፍረስና ህዝብ የመበደል ሴራ ግልፅ ሆኗል ያሉት ሊቀመንበሩ አሁን ዋናው ቀዳሚ ተግባራችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት በጋራ ማስቀጠል ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፓርቲው በፖለቲካና በሌሎች ጉዳዮች ልዩነት ቢኖረውም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አይደራደርም፤ በከሃዲና ተላላኪ ባንዳ አገር እንድትወረር አይፍቅድም፤ አባላትና ደጋፊዎቻችንን አስተባብረን እስከ ህይወት መስዋትነት እንፋለማለን ብለዋል፡፡

“ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በእልህ አጠናክሮ የሽብርተኛውን ቡድን እድሜ ማሳጠር ይኖርበታልም” ብለዋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል ወጣት መኮነን አሊ በሰጠው አስተያየት አሸባሪው ህወሓት እድሜ ልኩን የሰራው ድርብርብ ወንጀል አልበቃው ብሎ አገር ለማፍረስ የወጠነውን ሴራ ለማክሸፍ የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

መንግስት ያደረገውን አገር የማዳን ጥሪ ተቀብሎም የመሰረታዊ ውትድርና እና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች መሰልጠኑን ጠቁሞ፤ የከተማውን ሰላም ከማስበቅ ባለፈ ግንባር ዘምቶ ቡድኑን ለመደምሰስ ቆርጦ መነሳቱን ገልጿል።

ለሌላዋ ተጠባባቂ ኃይል ወጣት ገነት አራጌ በበኩሏ “ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ አገር ለማፍረስ የሚሰራን ሃይል በአጥንትና በደማችን መፋለም ግዴታችን ነው”ትላለች።

አሸባረው ህወሓትን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ወደ ግንባር ለመሄድ ወታደራዊ ስልጠና መውሰዷን ገልጻ፤ “ወጣቱን በማደራጀት የከተማውን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ለአገሬ ህይወቴን አሳልፌ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ብላለች፡፡

“እንኳን በውሸትና በሰው ደም የሰከረ ታሪካዊ ጠላታችንን ወያኔን ቀርቶ ዘመናዊ ትጥቅ ለታጠቀ የውጭ ኃይልም እንደማንበረከክ አባቶቻችን አስተምረውናል” ያለችው ወጣቷ ተደራጅተን የአባቶቻችን ታሪክ እንደግማለን ብላለች፡፡

ትላንት በተካሔደው የምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ አመራሮች፤ የሐይማኖት አባቶች ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም