ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገቡ

አዲስ አበባ  ነሐሴ 11 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ገቡ።
 ሠራተኞቹ የአገር ሕልውና ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሠራዊቱን ለመደገፍ ቁርጠኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከደመወዛቸው በተጨማሪ ደም እንደሚለግሱና በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

አገሩን ከጠላት ለመጠበቅ ሕይወቱን እየከፈለ ላለው ሠራዊት በደጀንነት እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

ሠራተኞቹ እስከ ግንባር በመሄድ ጭምር መስዋዕትነት ለመክፈልና ኢትዮጵያን ለማዳን ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

አገሪቷን ከገጠማት ችግር ለመታደግ በየአካባቢው ያሉ አጥፊዎችና ባንዳዎችን ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ክፉኛ እየተፈታተኗት በመሆኑ ሴራውን ለመቀልበስ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሰለፍ አለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም