ቀጥታ፡

ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም በአገር ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ በተደራጀ መልኩ መመከት ይገባል

አዲስ አበባ  ነሐሴ 11 /2013 (ኢዜአ) ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም በአገር ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ በተደራጀ መልኩ መመከት እንደሚገባ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
ዜጎች በአንድነት በመቆም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግን ጣልቃ ገብነት "በቃ" ማለት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያዘጋጀውና ትኩረቱን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል።

በውይይቱም ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የመጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩም አሸባሪው ህወሃት "በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ በምን መልኩ መመከት ይገባል?" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

ተሳታፊዎቹ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ የአገር ህልውና እና ሰላምን ማስጠበቅ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ይጠይቃል።

ከዚህ አኳያ መንግስት አሸባሪው የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመመከት ላስተላለፈው ጥሪ ዜጎች አበረታች መልስ መስጠታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪ ሃይልን ድል በመንሳት ለዓለም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ችቦ ያበራች አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ አሁን ደግሞ በኢኮኖሚው ዘርፍ ለውጥ በማምጣት ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ነጻነት አብነት የሚሆን ተግባር ማከናወን መጀመሯን ተናግረዋል።

ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያ ካለችበት ጂኦ - ፖለቲካ ጋር ተዳምሮ ለውጭ ጣልቃ ገብነት እንደዳረጋትም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም ዜጎች በአንድነት በመቆም የውጭ ጣልቃ ገብነት "በቃ" ማለት እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሸባሪው ህወሃት በመንግስት የቀረበለትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ የክህደት ጥቃት ከመፈጸሙ በተጨማሪ አሁን ላይ በትግራይ አጎራባች ክልሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙንም ነው የገለጹት።

የመከላከያ ሠራዊት ከራሱ በፊት ህዝብና አገርን አስቀድሞ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ለኢትዮጵያ ህልውና ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል "በጋራ በመቆም ለሠራዊቱ ደጀን መሆን አለበት፤ ከመንግስት ጎንም መሰለፍ ይገባል" ነው ያሉት።

ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በየአካባቢቢው ለሚገኙ የሠራዊቱ ቤተሰቦች ተገቢውን ክብርና ድጋፍ መስጠት እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የምርጫና ዴሞክራሲ ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ዛዲግ አብረሃም በበኩላቸው፤ መንግስት በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ዓይነት ችግሮች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

"የኢትዮጵያ መንግስት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ጋር ሰላም በመፍጠር እንዲሁም ጎረቤት ሱዳን አጋጥሟት የነበረውን ችግር በሰላም እንዲፈታ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ለሰላም ያለውን ዋጋ ለዓለም አሳይቷል" ብለዋል።።

"አሸባሪው ህወሃት ለሰላም የተዘረጉ እጆችን ወደ ጎን በመግፋት የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል እየተንቀሳቀሰ ነው፤ መንግስት ደግሞ አገር የማስጠበቅ ግዴታ አለበት" ነው ያሉት አቶ ዛዲግ።

በመሆኑም በጋራ በመቆም የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመጨረሻ ጊዜ መቀልበስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህን በማድረግም ከሽብር ቡድኑ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሹ የውጭ ሃይሎችን "የፈለጉትን ማድረግ እንደማይችሉ ማስገንዘብ አለብን" ብለዋል።

ዜጎች መንግስት የሚያስቀምጠውን አቅጣጫ በመከተል የህልውና ትግሉን በተደራጀና በተናበበ መንገድ መቀጠል እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።

በዜጎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ለማሳካት የሚሰሩ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ይህን በማድረግም በኢትዮጵያ ላይ እጅ በመጠምዘዝ ምንም ነገር ማሳካት እንደማይቻል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  ማስገንዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም