ወንድማማቾቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ አሸባሪዎችን በማክሰም ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ውትድርናን ተቀላቀሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወንድማማቾቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ አሸባሪዎችን በማክሰም ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ውትድርናን ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚጥሩ አሸባሪ ኃይሎችን በማክሰም 'ለሉዓላዊነቷ መጠበቅ በቁርጠኝነት ለመታገል ቆርጠናል' ይላሉ በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል መሰረታዊ ውትድርና ሰልጣኝ ወንድማማቾች ምልምል ወታደሮቹ።
ኢትዮጵያ እምቢ ለባርነት እምቢ ለጭቆና ብለው ሕይወታቸውን የከፈሉላት፤ በሕዝቦቿ አንድነትና ትስስር የተገነባች፤ ለአፍሪካና ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ቀንዲል ነች።
ሕዝቦቿ ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር በኋላቀር መሳሪያ በዱር በገደል አሳደው በአንድነት ለአገራቸው ሉዓላዊነት ታሪክ አይሽሬ ማህተም ከትበው ለልጅ ልጆቻቸው ነፃ አገር ያወረሱም ናቸው።
ለዚህ አኩሪ ገድል መገኘት ሕዝብ የመሪውን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ጠላቱን ለማጥፋት መወሰኑ ዓበይት ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ እስካሁን የቆመችው ሕዝቦቿ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በጽናትና በአንድነት ተጋድሏቸው መመከት በመቻላቸው መሆኑ ይወሳል።
አሁንም የአገር ጠላት የሆነውን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ተጋድሎ በርካታ ወጣቶች ከቀደምት አባቶቻቸው የተረከቧትን አገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በታላቅ ወኔ ትግሉን ተቀላቅለዋል።

ከአገሪቷ አራቱም ማዕዘናት የተመሙ የኢትዮጵያ ልጆች በተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላት ገብተው መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።
ኢዜአ "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ መቼም፣ የትም፣ በምንም" በሚል አገር ያቀረበችውን ጥሪ በመቀበል በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል የከተቱ ወንድማማቾችን አነጋግሯል።
ውልደትና እድገታቸው በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ ፍቼ ነው፤ መሰረታዊ ምልምል ወታደር ኢሳያስ ጌታሁን እና መሰረታዊ ወታደር ሽመልስ ጌታሁን።
ሰልጣኝ ወንድማማቾች አገር ሠላም ሆና ካላደረች ትምህርትም ሆነ ማንኛውም ነገር ሊኖር አይችልም ይላሉ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ በቁጭትና በወኔ ተቀብለው ሠራዊቱን መቀላቀላቸውንም ገልጸዋል።
ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ከገቡ በኋላም የአገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚሰጠውን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በሚገባ እየቀሰሙ መሆኑን ተናግረዋል።
የመሰረታዊ ምልምል ወታደር ሽመልስ ጌታሁን ታላቅ ወንድም ኢሳያስ ጌታሁን በአካል ብቃትና በኢላማ ተኩስ ስልጠናዎች "የኮከብ ተኳሽነት" ማዕረግ ተችሮኛል ብሏል።
ስልጠናውን አጠናቆ አሸባሪው የህወሓት ቡድን እያካሄደ ያለውን አገር የማፍረስ ተልዕኮ ለማክሰም በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልጿል።
ከወንድሙ ጋር ወደ ስልጠናው የመጡት ሽብርተኛውን ቡድን በማጥፋት ለአገራቸው ሉዓላዊነት መከበርና ለሕዝባቸው ሠላም መከታ ለመሆን እንደሆነም ተናግሯል።
መሰረታዊ ምልምል ወታደር ሽመልስ ጌታሁንም እርሱና ወንድሙ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ተወልደው ትምህርት ተከታትለው መጨረሳቸውን ገልጿል።
ሁለት እህቶችና ሶስት ወንድሞች እንዳሏቸው በመግለጽ ከአገር በላይ ምንም የለም በማለት አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመፋለም ወደ ማሰልጠኛ መግባታቸውን ነው የተናገረው።
የሚሰጣቸውን የውትድርና ሳይንስና ጥበብ የጠላትን ዓላማ ማክሸፍ በሚያስችል መልኩ እየቀሰሙ እንደሆነም አክሏል።
ወንድማማቾቹ 'ኑ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን እናጥፋ፤ የአገራችንን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ሉዓላዊነቷን እናስቀጥል' ሲሉም ለኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህቶቻቸው የጋራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።