ኮርያ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከላከያ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ኮርያ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከላከያ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11/2013 (ኢዜአ) የኮርያ የዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) 40 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገባቸው የኮቪድ 19 መከላከያ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ የኮሮናቫይረስ መከላከያ የህክምና ቁሳቁስን ጨምሮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል /ማስክ/ እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ /ሳኒታይዘር/ አካቷል።
ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ለፌደራል የቴክኒክ ሙያና ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲና ለኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ ነው ተብሏል ድጋፉ።
ድጋፉ ኤጀንሲው ለተቋማቱ በሚያደርገው የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ ውስጥ አንድ አካል ሲሆን ከ7 ሺህ በላይ የተቋማቱ ሠራተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
በፌደራል የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ የሴክተር ፖሊሲና ስትራቴጂ ዳይሬክተር አቶ መለሰ ይመር፤ ድጋፉ ኤጀንሲው ወረርሺኙን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
በመሆኑም ኮይካ ወረርሺኙን በመከላከል ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና እንዲሰጥ ለማስቻል መሰል ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
የኮርያ የዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሊ ብዩንግዋ በበኩላቸው የኮይካ ድጋፉ ለተለያዩ ተቋመት መሰል ድጋፎች መደረጋቸውን አንስተዋል።
ኮይካ ለተቋማት የሚያደርገው ድጋፍም ወረርሺኙን ለመከላከል በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራውን ሥራ በማጠናከርና በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የኮርያ የዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2020 እስከ 2026 ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት አቅም ግንባታ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መድቧል።
ኮይካ በአውሮፓውያኑ ከ1995 ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።