አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደር መኖሪያ መንደሮች እንዲወድሙ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደር መኖሪያ መንደሮች እንዲወድሙ አድርጓል
ነሀሴ 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደር መኖሪያ መንደሮች እንዲወድሙ ማድረጉን የእንግሊዙ ዘ ቴግራፍ ባደረገው ምርመራ አመለከተ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል ትንኮሳ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሮች የመኖሪያ መንደሮችን ሆን ብሎ እንዲወድሙና እንዲዘረፉ ማድረጉን ዘገባው አመልክቷል።ጋዜጣው ዲ ኤክስ ኦፕን ኔትዎርክ ከተባለ የእንግሊዝ የሳተላይት መረጃዎች ጥናትና ትንተና ተቋም ጋር በመሆን የሰራው ምርመራ እንደሚያመለክተው በአማራ ክልል ቆቦ ሮቢት አካባቢ አገምሳ ተብሎ በሚታወቀው መንደር የነበሩ የሳር ጎጆዎች አሸባሪው ባደረገው ጥቃት ሙሉ ለሙሉ በእሳት የወደሙ መሆኑን አመልክቷል።
የአካቢው ነዋሪዎችም ራሳቸውን ለመከላከል ያደረጉት ጥረት አልተሳካም ብሏል።አገምሳ ወደሚባለው መንደር የገቡት የአሸባሪው ታጣቂዎች ያልታጠቁና ሰላማዊ ሰዎችን ያለምንም ምህረት እየገደሉና ንብረት ሲያወድሙ መቆየታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ በዚህ ግጭት ብቻ ከ200 ሺህ በላይ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል።በጥላቻና በቀል ተሞልተው የመጡት የአሸባሪው ሃይሎች ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም የአርሶአደሮች መኖሪያ መንደሮችን ሲደበድቡ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።
በሰሜን ወሎ አካባቢም ተመሳሳይ ጥቃቶች መድረሳቸውን የአይን እማኞች መናገራቸውን በዘገባው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ያልነበረባቸውን ቦታዎች እየመረጡ ጥቃት ሲያደርሱ የነበሩት የአሸባሪው ታጣቂዎች ቤት ለቤት እየዞሩ በሚያደርጉት ፍተሻ ያገኙትን ሁሉ ሲዘርፉና ሲገድሉ መሰንበታቸውን ያተተው ዘገባው ከግድያው ባሻገርም የመኖሪያ ቤቶችና የተከማቹ የምግብ እህሎች ላይ እሳት በመለኮስ ማውደማቸውን ገልጿል።ከወራት በፊት መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ተደራሸ እንዲሆንና የእርሻ ስራም የዝናቡን ወቅት ተከትሎ እንዲጀመር በሚል የተናጥል የተኩስ ማቆም እርምጃ ቢወስድም የአሸባሪው ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ወረራዎችን መፈጸሙን ዘገባው አስታውሷል።