እንግሊዝ 500 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ለኢትዮጵያ ሰጠች - ኢዜአ አማርኛ
እንግሊዝ 500 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ለኢትዮጵያ ሰጠች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11/2013 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከእንግሊዝ የተሰጠውን 500 ሺህ ዶዝ አስትራዜኒካ የኮቪድ-19 ክትባት ተረከቡ።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ የተጓጓዘውን ክትባት በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር አሌክስ ካሜሮን ናቸው ለዶክተር ሊያ ታደሰ ያስረከቡት።
ዶክተር ሊያ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተደራሽ ለማድረግ በስፋት እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ዕድሜው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ሆኖ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንዲከተቡ አሳስበዋል።
ከእንግሊዝ የተሰጠው ድጋፍ የመጀመሪያውን ክትባት ወስደው ሁለተኛውን ዙር በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ሰዎች መስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ የኮቪድ ክትባት ቢወስድም ለአፍታም ቢሆን መዘናጋት የለበትም ያሉት ዶክተር ሊያ ወረርሽኙን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች ሊተገበሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ባለፉት ሁለት ሣምንታት በኢትዮጵያ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን አስታውሰው፤ ኅብረተሰቡ ራሱን ከመጠበቀ ለአፍታም እንዳይዘናጋ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሯ የኮቪድ ክትባቶቹን ድጋፍ ላደረገው የእንግሊዝ መንግስት እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ የሎጀስቲክ ድጋፍ ላደረገው የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንግድ የኮቪድ ክትባቶችን በማጓጓዝ ላበረከተው አስተዋፅኦም እንዲሁ።
የኢትዮጵያና እንግሊዝን ወዳጅነት የጠቀሱት በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር አሌክስ ካሜሮን አገራቱ በተለይ በጤናው መስክ በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከጤና ሚኒስቴርና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።
የክትባት ድጋፉ እንግሊዝ በቡድን 7 አባል አገራት ስብሰባ ለዓለም ለመስጠት ቃል ከገባችው 100 ሚሊዮን የአስትራዜኒካ የኮቪድ ክትባቶች በተለይ ለአፍሪካና እስያ ከምትሰጠው አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲልም አሜሪካ የኮቪድ-19 ክትባት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጓ ይታወቃል።