ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት ከሆነው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጋር ግንባር መፍጠሩ ህዝብ ለማጥፋት መዘጋጀቱን ማረጋገጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት ከሆነው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጋር ግንባር መፍጠሩ ህዝብ ለማጥፋት መዘጋጀቱን ማረጋገጫ ነው
ነሐሴ 11/2013 (ኢዜአ) ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት ከሆነው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጋር ግንባር መፍጠሩ ህዝብ ለማጥፋት መዘጋጀቱን ማረጋገጫ ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ወርቅነሽ ብሩ ገለጹ።
በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል ምልምል ወታደሮች የአገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅና ጠላትን በመፋለም የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።
የኪነ ጥበብ ሰዎች በስፍራው በመገኘት "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ መቼም የትም በምንም" የሚለውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ስራዎቻቸውን ለሰልጣኞቹ አቅርበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ወርቅነሽ ብሩ፤ ሸኔ የኦሮሞ ብሎም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ዘላለማዊ ጣላት ከሆነው አሸባሪው ህወሃት ጋር ግንባር በመፍጠር ህዝብ ለማጥፋት እየሰራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቶች እነዚህን አገር አፍራሽ አሸባሪ ቡድኖች ማጥፋት አለባቸው ብለዋል።
የአሸባሪ ቡድኖቹ ዓላማ "እኔ ከሞትኩ..." በሚል ኢትዮጵያ እንዲትጠፋ ከተለያዩ የውጭ ሃይሎች ጋር ባንዳ ሆነው እያገለገሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ኦሮሞ ህዝብ እራሱን በራሱ ማስተዳደር የሚችል ማንነት ያለው ታላቅ ህዝብ መሆኑን ጠቅሰው ሸኔ ህዝቡን በመውጋት አከባቢውን የሽብር ቀጠና ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
የጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ጦምሲ ደፊታሞ፤ በስልጠና ላይ የሚገኙት ምልምል ወታደሮች በፍፁም አገር ወዳድነትና የጀግንነት ወኔ የሰነቁ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የአሸባሪዎች ስጋት በመመከት ለድል አድራጊነት እየተዘጋጁ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከያኒያኑም ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት "መቼም የትም በምንም" ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አሸባሪውን የህወሃት ቡድን በመደምሰስ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁነታቸውንም ገልጸዋል።
በዝግጅቱ ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮነኖች፣ አርቲስቶችና ሌሎችም ተገኝተዋል።