ቡድኖቹ ያደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸውን አቋም በግልጽ አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
ቡድኖቹ ያደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸውን አቋም በግልጽ አሳይቷል
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 11/2013 (ኢዜአ) አሸባሪቹ ህወሃትና ሸኔ በቅርቡ ያደረጉት ስምምነት በህዝቦች ላይ የፈፀሙትን ግፍና ሰቆቃ በመድገም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያላቸውን የፀና አቋም በግልፅ ያሳየ መሆኑን ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመለከቱ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የብልፅግና እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ፓርቲዎች ለኢዜአ እንዳስረዱት ፤ ህወሃትና ሸኔ ያደረጉት ስምምነት በይዘቱ አዲስ ያልሆነና መነሻውም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ካላቸው የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነው።
የአብን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ፤የሁለቱ ፅንፈኛ ቡድኖች የፖለቲካ መርህ በጥላቻና ሀገር በማፍረስ ላይ እንደሚመሰረት ገልጸው፤ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጠሉና አማራን ተወቃሽ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች በኢትዮጵያ ታሪክና ጀግኖች ላይ የማይስማሙ፤ ሀገርንና ሀገረ መንግሥቱን በመካድና በመጥላት የጋራ አቋም መያዛቸውን አመልክተዋል።
ቡድኖቹ ያደረጉት ስምምነት ህዝብን የመበደል፣ የመጨቆንና የመግደል የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው አለመለወጡን በትክክል አሳይቷል ነው ያሉት አቶ ጣሂር።
ስምምነቱ በአማራ ህዝብ ቅንጣት ታክል ችግር አያመጣም ያሉት አቶ ጣሂር፣ በዚህ ወቅት የሃይል አሰላለፋቸውን ማሳወቃቸው የትግሉን አቅጣጫ ለመቀየስ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
"የቡድኖች ስምምነት ሀገርን የማፍረስ የመጨረሻ ግብ በግልፅ ከማሳየቱም ባለፈ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እድል እንዳይኖራቸው የሚያነቃ ነው" ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ የአማራ ክልል ምክትል ሃላፊ አቶ ፍሥሐ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች ጥምረት ከትናንቱ ባህሪያቸው የተለየ ለዛሬ የሚሆን የፖለቲካ ሃሳብ እንደሌላቸው ያሳያል ይላሉ።
ጥምረቱ አሸባሪው ህወሃት በሥልጣን በነበረበት ወቅት በአሽባሪነት ፈርጆ ሲያሳድደው ከነበረ ቡድን ጋር መሆኑ
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ለማሰባሰብ የሚያደርገውን ጥረት በግልጽ አሳይቷል ነው ያሉት።
ቡድኖቹ ባለፉት ዓመታትም በሀገሪቱ ግድያ፣መፈናቀል፣ዝርፊያና ነውጥ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አቶ ፍሥሐ አስታውሰዋል።
እነዚህ አሸባሪዎች ኢትዮጵያን ለመበዝበዝ፣ ህዝቦችን የመበታተንና በጠላትነት ፈርጀው ለማጥቃት መጣመርን መምረጣቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ ላይ ጠላት በተነሳ ጊዜ እንዴት እንደሚመክት ያውቃል ያሉት ምክትል ሃላፊው፤ እነዚህ ፅንፈኞችን በተባበረ ክንድ ለመደምሰስ እየተረባረቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ቡድኖቹ ቴክኒካዊ ካልሆነ በስተቀር በአስተሳሰባቸው አንድ ናቸው የሚሉት ደግሞ የኢዜማ አባል አቶ መስፍን አጥላው ናቸው።
የከደርግ ውደቀት በኋላ እንኳን አብረው ለመስራት ባለመቻላቸው የተለያዩ ፅንፈኛ ቡድኖች መሆናቸውን አመልክተው፣ዛሬ ያደረጉት ስምምነት ሀገር የማፍረስ የጋራ ተልዕኮ በመያዛቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ሁለቱም ኢትዮጵያን በማፍረስ ህዝቦቿን ለችግርና ስቃይ ለመዳረግ የተነሱ ሴረኞች በመሆናቸው የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ቡድኖቹን መደምሰስ ይገባናል ነው ያሉት።
ህወሃትና ሸኔ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት መፈረጃቸው ይታወሳል።