''ካልሞትኩ ከማገኘው ግድቡ እስኪጠናቀቅ እለግሳለሁ'' - ኢዜአ አማርኛ
''ካልሞትኩ ከማገኘው ግድቡ እስኪጠናቀቅ እለግሳለሁ''
ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 11/2013 (ኢዜአ) ''ካልሞትኩ ከማገኘው ግድቡ እስኪጠናቀቅ እለግሳለሁ'' አሉ አዛውንቱ የጥበቃ ሠራተኛ።
የአዛውንቱ አካላዊ ብቃትና አዕምሯዊ ፍጥነት ላየ ዕድሜያቸውን ይጠራጠራል፡፡
ዕድሜያቸው 80 ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት አዛውንቱ ፤ በድሬዳዋ አንድ ሆቴል ከረንቦላ እያጫወቱና የሆቴሉንም ግቢ እየጠበቁ በሚያገኙት ገቢ ነው የሚተዳደሩት።
ምኞታቸው የህዳሴ ግድብን በአካል ተገኝተው መጠበቅ ነበር፤ አልተመቻቸላቸውም እንጂ ፤ የዘመናት ቁጭታቸው ደግሞ አባይ ተገድቦ በማየታቸው የሕይወታቸው ታላቁ ደስታና እፎይታ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
''ሃብት የለኝም፤ ከዚህች ከማገኛት ገንዘብ የሀገሬን የብልጽግና ተስፋ የሆነው ግድቡ እንዲጠናቀቅ ቦንድ ገዝቻለሁ፤ በነጻም መቶ ብር ድጋፍ አድርጌያለሁ'' ብለዋል፡፡
''ካልሞትኩ ከማገኘው ግድቡ እስኪጠናቀቅ እለግሳለሁ'' ይላሉ አቶ ወንደሰን ደምሴ፡፡
የአሁኑ ትውልድ ከስደት ተገላግሎ በሀገሩ እንዲኖር ግድቡን ተረባርቦ መጨረስና እንደ ዓይን ብሌኑ መጠበቅ ግዴታው ነው ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋ የሆነውና ወጣቶችን ከስደት የሚያድነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከምናገኛት ደግፈንና ገንብተን እንጨርሰዋለን የሚሉት ደግሞ በከተማዋ በአነስተኛ ሥራዎች የተሰማሩ ነዋሪዎች ናቸው።
የግድቡን ግንባታ ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን የአካባቢያቸውን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንወጣለንም ይላሉ፡፡
ወጣት ታደለ ካሣና ጓደኞቹ ለሥራ ፍለጋ ድሬዳዋ ከመጡ ጥቂት ዓመታት አስቆጥረዋል፤ አሁን ትጋታቸው ሰምሮ አሻንጉሊቶች እያደሱና እያበጁ ይሸጣሉ፡፡
ወጣቱ ሥራ ያጣው ብዙ የሥራ ዕድል ባለመኖሩ ነው፤ የሀገራችን የብልጽግና መሠረት የሆነው የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ግን ለኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ እንደሚፈጠር እምነቱን ይገልጻል፡፡
''ቀደም ሲል ገንዘብ የማግኘት ዕድል አልነበረንም አሁን ግን ከምናገኛት ላይ የግድቡን ቦንድ ለመግዛት ወስነናል'' ይላል ታደለ፡፡
''ግድቡ ለሀገራችንና ለወጣቶች ትልቅ ተስፋ ነው'' ሲልም ነገን ያሳየናል፡፡
የሥራ ባልደረባው ኦላና ፋንታሁን በበኩሉ ፤ከድጋፉ በተጨማሪ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ተሳትፎ እንደሚያደርግና ካለ ሰላም የሚሆን ነገር የለምና ብላል።
ሌላው ጫማ በማደስ ሥራ ላይ 15 ዓመታት እንዳሰለፉ የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ በቀለ ፤''ግድቡ ለብዙ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና ለሀገር መበልጸግ ከሚያመጣው ዕድል በተጨማሪ እኔና ሌሎችም ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያደርገናል ይላሉ።
''የግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ከምናገኛት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እናደርጋለን ፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ እኔም ኤሌክትሪክን በቀላል ዋጋ በመጠቀም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የጫማ ማሽን ይኖረኛል'' ብለዋል፡፡
''ግድቡ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት የጫማ ማምረቻ ባለቤት እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ፤ ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ'' ሲሉም ተስፋቸውን ይገልጻሉ።
''ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ ነው፤ለሶስት ጊዜ ቦንድ ገዝቻለሁ፤ አሁን ደግሞ ዋንጫው ከተማችን ስለሚገኝ እቀጥላለሁ'' ብለዋል፡፡
ይሄ ሁሉ ምኞታቸው ዕውን የሚሆነው ሀገርን ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶችን በአንድነት በማጥፋት ሰላም ሲኖር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ዜጎች በየአካባቢያቸው ሀገር አፍራሾችንና ሰላም አደፍራሾችን ከነተላላኪዎቻቸው በመደምሰስ በጋራ ሀገርን ወደ ከፍታ ለማሻገር መትጋት እንዳለባቸው አቶ ሙሉጌታ አመልክተዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የድሬዳዋ የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ፤ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ መግባቱን ተከትሎ የነዋሪዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ መድረኮች እያመቻቹ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሐረሪ ክልል ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር የገባው ባለፈው ወር ነው፡፡
ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው ግድብ ባለፈው ወር ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተከናወነ ሲሆን፤በሁለት ተርባይኖቹ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይጀምራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡