አሸባሪው ህወሓት የከፈተብንን ጦርነት ለመመከት ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሃብት የማሰባሰብ ስራ የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት የከፈተብንን ጦርነት ለመመከት ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሃብት የማሰባሰብ ስራ የሚበረታታ ነው
ነሀሴ 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) "አሸባሪው የህወሀት ቡድን ሃገራችንን ለመበታተን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሃብት የማሰባሰብ ስራ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው" ሲሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ተናገሩ።
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዳያስፖራው ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉም ተገልጿል፡፡
በጣሊያንና አካባቢዋ በሚገኙ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ እትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።
በጣሊያን የኢፌዴሪ ኤምባሲ አስተባባሪነት በተዘጋጀዉ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በጣሊያንና አካባቢዋ በሚገኙ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረጉት ላሉት ጠንካራ ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
አክለውም አሸባሪው የህወሀት ቡድን ሃገራችንን ለመበታተን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ኢትዮጵያውያን በያሉበት ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን መቆማቸውን አንስተው፣ ከዚህ አንጻር ዳያስፖራውም እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሃብት የማሰባሰብ ስራ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ገልጸዋል።
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዳያስፖራው ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ የሃገር አለኝታነቱንና ለመከላከያ ሃይላችን የሞራል ምንጭ መሆኑን ማሳየቱን ጠቅሰው፣ በዳያስፖራው ዘንድ በታየው መነሳሳትና ከፍተኛ የሃገር ፍቅር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሃገር መከላከያ ሰራዊታችንን ለመደገፍ ከታቀደው አንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰብ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በጣሊያን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳም በበኩላቸው በሃገራችን ስላላው ወቅታዊ ሁኔታ ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ የሰጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የገጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ የቀጠለች ሃገር መሆኗን አስገንዝበዋል።
አክለውም በአሸባሪው ህወሃት የተከፈተብንን ጦርነትና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለመመከት ዳያስፖራው በአንድነት እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል። ዳያስፖራው ገንዘቡን ወደ ሃገር ቤት በህጋዊ መልኩ ብቻ በመላክ የሃገሩን አቅም እንዲያጠናክር ጠይቀው፣ የዳያስፖራ ማህበራትን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችም እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን ኤጄንሲው አስታውቋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላትም በአሸባሪው ቡድን የተፈጸመው ወረራ የዳያስፖራውን አንድነት እንዳጠነከረው ገልጸው፣ በቋሚነት ሃገራቸውን መገደፍ ስለሚችሉበት ሁኔታና ከኤምባሲ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ላነሷቸው ጥያቄዎች ከመድረክ ምላሾች ተሰጥተዋል።