አሸባሪው ህወሃት ከሀገራችን እስኪወገድ እረፍትና እንቅልፍ የለንም-- አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት ከሀገራችን እስኪወገድ እረፍትና እንቅልፍ የለንም-- አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ነሐሴ 10/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ከሀገራችን ተወግዶ የሠላም አየር እስከ ሚረጋገጥ ድረስ የሲዳማ ህዝብና መንግሥት እረፍትና እንቅልፍ የለንም ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ህወሓት በ27 ዓመታት የስልጣን ቆይታው ሀገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሲበዘብዝና የህግ የበላይነትን በመጣስ ህዝብን ሲበድልና ሲጨቁን መቆየቱን አወስተዋል።
በዚህ የተማረረው የሀገሪቱ ዜጋ ከዳር ዳር በመነቃነቅ ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ ቢጥለውም የዘረፈውን ሀብት እንኳን አርፎ መብላት ተስኖት አሁንም እንደለመደው ተመልሶ ሀገሪቱን ለመበዝበዝና ለማጥፋት እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።
የአሸባሪውን መራራነት ቀምሶ ያየው የሲዳማ ህዝብም የጥፋት ተልዕኮውን ተቀናጅቶ መግታት እንዳለበት በማመን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በተሰጣቸው ግዳጅ ላይ እየተፋለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው 4 ሺህ የሚጠጉ የክልሉ ወጣቶችም በፍቃደኝነት ለመዝመት ወታደራዊ ስልጠና እየተከታተሉ ነው ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊቱን በሰው ሃይል ከማጠናከር ባለፈ በቁሳቁስ ለመደገፍ በየደረጃው የሚገኙ ባለሀብቶች፣ወጣቶች፣ሌላው የህብረተሰብ ክፍልና የመንግስት መዋቅር ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
በሀገራችን ላይ የሚቃጣውን ማንኛውንም ጥቃት በሚገባ ለመመከት የክልሉ ህዝብና መንግሥት በቁጭትና እልህ እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ ፤አሸባሪው የህወሃት ረዝራዥ ከሀገራች ምድር ተወግዶ የሠላም አየር እስከ ሚረጋገጥ ድረስ የሲዳማ ህዝብና መንግሥት እረፍትና እንቅልፍ አይኖራቸውም።
የሸኔና ህወሃት ጥምረትም ተያይዞ ለመጥፋት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተለይ የነዚህን ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ ማናቸውም ቡድንና ግለሰብ ላይ ያለምህረት ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሃት በዘረፈው ገንዘብ ብዙ ሰዎችን በመግዛቱ ለምን ይነካል የሚሉ ጠበቆች በሲዳምኛ የሚናገሩትን ጭምር ለማየትና ለመስማት ችለናል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በማንኛውም መልኩ የጥቅም ተጋሪ በመሆን ህዝብን ለማደናገር የሚሞክሩ የአሸባሪውን ቡድን ደጋፊዎች ካሉ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ከህልውናው ዘመቻ በተጓዳኝ የክልሉን የልማት ስራዎች ለማስፈጸም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ የወቅቱ ዋንኛ ስራ የሆነውን የመኸር ግብርና ልማት አምራች አርሶ አደሩን በማንቀሳቀስ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።