ቀጥታ፡

ለሀገራችን የምንሰስተው ነገር የለም--የስልጤ ዞን ነዋሪዎች

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 10/2013 (ኢዜአ) የአሸባሪው ትህነግ ሴራ ከሽፎ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እስኪረጋገጥ ድረስ የምንሰስተው ነገር የለም ሲሉ የስልጤ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ ።

 ''እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ!'' መሪ ሀሳብ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍና አጋርነት ለመግለጽ የተዘጋጀ  ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር በወራቤ ከተማ ተካሂዷል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ ከድር በወቅቱ፤ አሸባሪው ትህነግ ሀገርን ለማፈራረስ የሚያካሂደውን ጦርነት ለማስቆም ታሪካዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።

የዞኑ ሕዝብ ሽብርተኛውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚፋለመውን መከላከያ ሰራዊት ለመደገፍ  ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ  በጥሬ ገንዘብና  ዓይነት  አስተዋጽኦ ማድረጉነ  አስታውቀዋል።

ሠራዊቱ የሀገር አንድነት ለማስከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሕዝቡ  አቅሙ በሚችለው መንገድ እንዲደግፍን እንዲቀጠልም መልዕክት አስተላለፈዋል።

የዞኑ ሕዝብ አገር ለማዳን እየተፋለመ ላለው መከላከያ ሠራዊት ደጀንነቱን እያሳየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የዞኑ  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቀድሩ አብደላ ናቸው።

መከላከያ ሠራዊትን በሰው ሃይል ለማጠናከር ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች በፈቃዳቸው ሠራዊቱን መቀላቀላቸውን ጠቅሰዋል።

በመረሃ  ግብሩ ከተሳተፉት መካከል የወራቤ ከተማ ነዋሪው ወጣት ነጃ ረዲ ሀገርን ከወራሪና ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ለማድረግ መዝመት እንደሚፈልግ ገልጿል።

''ለመከላከያ ሠራዊት ለመስጠት የምሰስተው ምንም ነገር የለኝም'' ብሏል።

የስልጤ ዞን  ወጣቶች ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ውላን ናሙዝ በበኩሉ፤ ሽብርተኛው ትህነግ ከምዕራባዊያን በሚያገኘው እርዳታ የሚፈጽመውን ወንጀል ታሪክ አይረሳውም ብሏል።

በሀገር ሰላም እንዲሰፍን የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን አስታውቋል።

መርሃ ግብሩ የስፖርቱ ማህበረሰብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ታስቦ  መዘጋጀቱን የደቡብ ክልል ስፖርት   ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብሩክ ቡናሮ ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ ሀገርን ለማዳን የሚካሄደው የህልውና ዘመቻ ድጋፉን በተግባር እያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች የደም ልገሳም አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም