ሰዎችን በማገት፣በማሰቃየትና ገንዘብ በመቀበል ወንጀል የፈፀሙ 4 ግለሰቦች በእድሜ ልክ እስራት ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
ሰዎችን በማገት፣በማሰቃየትና ገንዘብ በመቀበል ወንጀል የፈፀሙ 4 ግለሰቦች በእድሜ ልክ እስራት ተቀጡ
ነሀሴ 10/2013 (ኢዜአ) ግለሰቦቹ መቀመጫቸውን ሊቢያ ሀገር በማድረግ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሱዳን ዜግነት ያላቸው ሰዎችን አግቶ በማስቀመጥ ወደ ቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወል እያንዳንዳቸው 1 ሺ አምስት መቶ ዶላር እንዲከፍሉ ማድረጋቸውን ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ደርሶባቸዋል፡፡
ግለሰቦቹ የታጋቾቹን እጅና እግር አስሮ በመግረፍና በውሃ ጥም በማሰቃየት እንዲሁም በሚጠጡት ውሃ ላይ ጋዝ በመጨመር የስምንት ሰዎች ህይወት በግፍ እንዲያልፍ አድርገዋል ተብሏል፡፡
ታጋቾቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወልና የስቃይ ድምፃቸውን በማሰማት ቤተሰብን ቤት፣መኪና እና ሌሎች ንብረት በማሸጥ ገንዘብ እንዲላክላቸው ማድረጋቸውና የተጠዩቁት ገንዘብ ያልሞላላቸው የታጋች ቤተሰብ ደግሞ ከሰው ለምነው ያገኙትን ገንዘብ ቢከፍሉም ህይወት መታደግ እዳልቻሉ በወንጀል ምርመራ ቢሮ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የምርመራ ክፍል ገልጿል፡፡
የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ለ4 ወራት ከምርመራ ቡድኑ ጋር ተቀናጅቶ ባከናወነው የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክሱን ከተመለከተ በኋላ ግለሰቦቹ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ኪዳኔ ዘካሪያስ የተባለው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እና በ1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ መቀጮ፣አማኑኤል ይርጋን በ18 ዓመት ፅኑ እስራት፣ሲሳይ ወዳፍይን በ16 ዓመት እንዲሁም ሳባ መንደር የተባለውን በ12 ዓመት እና በ75 ሺህ ብር መቀጮ እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡
መሰል የወንጀል ድርጊቶች ሲፈፀሙ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ከፍለው ልጆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ከመላክ እንዲቆጠቡ ሲል የወንጀል ምርመራ ቢሮው መልዕእክቱን ማስተላለፉን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡