ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የመጣውን አሸባሪ በድን ለመመከት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንቆማለን--የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የመጣውን አሸባሪ ቡድን ለመመከት በሚደረገው ጥረት ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሚቆሙ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ሰራተኞች ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት ከ100 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ 40 በጎችን ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉንም ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረክበዋል፡፡

በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ቅጥር ግቢ በተደረገው የርክክብ መርሃ ግብር ላይ የአካል ጉዳተኞች ተወካዩች፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ወይንሸት ሙሉሰው፤ አካል ጉዳተኞች የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚደረገው ጥረት አካል ናቸው ብለዋል፡፡

በህወሃት አሸባሪ ቡድን በአገር ህልውና ላይ የተደቀነውን ችግር ለመመከት የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል አጋርነታቸውን ያስመሰከሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው የሀገር ሰላም ሲደፈርስ ቅድሚያ ተጠቂ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች እንደ መሆናቸው ለሀገር ሰላም መጠበቅ ቅድሚያ ዘብ እንቆማለን ብለዋል።

ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ህይወቱን ለሚሰጠው የመከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም በዛሬው እለት ከ100 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ 40 በጎችን ድጋፍ አድርገዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የህብረት ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የፋይናንስ ዳይሬክተር ብርጋዴል ጀነራል አስረስ አያሌው ድጋፉን በመረከብ አካል ጉዳተኞች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ባለው ድጋፍ ከሰራዊቱ ጎን መሆናቸውን ያረጋገጡበት አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ይዞ ከመስራት ውጭ የህዝብን ሰላምና ልማት አረጋግጦ አያውቅም ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ፌዴሬሽኑ ለሰራዊቱ ያደረገው ድጋፍ በሀገሪቱ ያሉ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞችን በመወከል መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም