በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያውያንና የማህበረሰብ ድርጅቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያውያንና የማህበረሰብ ድርጅቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው
ነሀሴ 10/2013 (ኢዜአ) በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን፣ የማህበረሰብ ድርጅቶችና አገር ወዳድ ግለሰቦች ተነሳሽነት በኢትዮጵያ በተፈጠረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው።
በኖርዌይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተባበሪ ኮሚቴ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የድጋፍ ማሰባሰቡ ከተጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡን ገልጿል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን የመንግስትን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በአማራና በአፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራ በርካታ ንጹናንንና ህፃናትን ከመግደሉ በተጨማሪ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል።
አሸባሪ ቡድኑ ወረራ ባደረገባቸው አካባቢዎች ንጹሃንን ከመግደልና ማፈናቀል ባለፈ በግለሰቦችና በመንግስት ተቋማትም ሀብትና ንብረት በመዝረፍ ስራ ላይ ተሰማርቷል።
በዚህም በአማራና አፋር ክልሎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ400 ሺህ በላይ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
በመሆኑም በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ ድርጅቶች የሲቪክ ማሐበራትና አገር ወዳድ ግለሰቦች ተነሳሽነት በኢትዮጵያ በተፈጠረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።
በኖርዌይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተባበሪ ኮሚቴም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሌት ተቀን በሚጥሩ ቡድኖች ምክንያት ሰብዓዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በህወሃት አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን መከራና ችግር በመጋራት ለወገን አለኝታ መሆናቸውን ለማሳየት የተጀመረ መሆኑን ኮሚቴው ገልጿል።
በኖርዌይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ድሪባ ኩማ፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን የስራቲጄክ ሎጀስቲክ ሴክተር ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሀሰን የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተደርጓል።
አምባሳደር ድሪባ ኩማ እንዳሉት በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ተነሳሽነት የታላቁ ህዳሴ ግድብና የኮቪድ 19 በሽታን ለመከላከል ላደረጉት ድጋፍ እውቅና ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደምም ለተፈናቃዮች ድጋፈ ማድረጋቸውን አስታውሰው አሁንም ኢትዮጵያ በገጠማት ፈተና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፤ ኤምባሲውም በማንኛውም መንገድ ከጎናቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።
የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን የስራቲጄክ ሎጀስቲክ ሴክተር ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሀሰን በኢትዮጵያ ለተፈጠረው መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውሰ ምላሽ ለመስጠት በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ዳያስፖራው በኢኮኖሚ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ያበረከተውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያን በተለያዩ ዘርፎች በማገዝ የዜጎች አለኝታ የሀገራቸው ደራሽ እንዲሆኑም አሳስበዋል።
በኖርዌይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተባበሪ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት ወዲህ በተጀመረው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 204 ሺህ 188 የኖርዊጅያን ክሩነር ወይም ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡን ገልጿል።
በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ ድርጅቶች ሲቪክ ማህበራትና አገር ወዳድ ግለሰቦችም በተሰማሩበት ዘርፍ ማህበረሰቡን በማስተባበር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።