ቀጥታ፡

በ2 የሥልጠና ማዕከሎች ለምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች የኪነ-ጥበብ ትርኢት ቀረበ

ነሐሴ 9/2013(ኢዜአ) በጦላይ እና በአዋሽ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ለሚሰለጥኑ ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች የማነቃቂያ የኪነ-ጥበብ ትርኢት ቀረበ።

ሠልጣኞቹ የአሸባሪዎቹን የሕወሃትና የሸኔ አገርን የማፍረስ የጥፋት ዓላማ አምክነው ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

 በጦላይ እና በአዋሽ ማሰልጠኛ ማዕከሎች ለሚሰለጥኑ ምልምል  መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች የማነቃቂያ የኪነ-ጥበብ ትርኢት ዛሬ ቀርቧል።

በዝግጅቱም ከብሔራዊ ትያትርና ከኦሮሚያ ባህል ማዕከል የተውጣጡ ከያኒያን፣ ኮሜዲያንና ሙዚቀኞች የጥበብ ሥራቸውን ለምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰልጣኞች አቅርበዋል።

ለመከላከያ ሠራዊቱ ደጀን ለመሆን በተካሄደው የኪነ ጥበብ ዝግጅት ላይ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ወርቅነሽ ብሩና የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሠልጣኝቹ የአሸባሪዎቹን የሕወሃትና የሸኔ አገርን የማፍረስ የጥፋት ዓላማ ማምከን አለባቸው።

በተለይም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን አንድነት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ለመፋለም ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት።

የጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጦምሲ ደፊታሞ፣ ሠልጣኞቹ ከኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ተመው ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሉ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ሠልጣኞች የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ በመከታተል የውስጥና የውጭ ሴራ በማክሸፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደሚያስጠብቁ ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።

ሃሳባቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ ቀደምት የጥበብ ባለሙያዎች የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ወደ ግንባር ጭምር በመዝመት ለሠራዊቱ ደጀን መሆናቸውን እንደሚያረጋግጡም ተናግረዋል።

ሠልጣኞቹ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የአገራቸውን ሉዓላዊነት በማስቀጠል ለሕዝብ ሰላምና መረጋጋት እንደሚታገሉ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ''ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ መቼም፣ የትም፣ በምንም'' የሚለውን አገራዊ ጥሪ ተከትሎ ነው ለምልምል መሰረታዊ ወታደሮች የጥበብ ሥራቸውን ያቀረቡት።

በተመሳሳይ ዜና በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትያትር ቤቶች የተውጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በአዋሽ ማሰልጠኛ ማዕከል ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሠልጣኞችን በተለያዩ የጥበብ ሰራዎች አነቃቅተዋል። 

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በሙያቸው ምልምል መሰረታዊ ወታደር ሰለጣኞችን ከማነቃቃት ባለፈ ግምባር ድረስ በመሔድ ለመዋጋት ዝግጁ ናቸው።

"በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ከአገር ጎን መቆም መታደል ነው" ያሉት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፤ በሁሉም መልኩ አገርን ለማዳን መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

በቀጣይ በተለያዩ ግምባሮች እንደሚሄዱ የተናገሩት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ፤ ሌሎች የእነርሱን መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የማዕከሉ አዛዥ ኮለኔል ተረፈ ጬሪሶ በበኩላቸው፤ የቀረቡት የኪነ ጥበብ ስራዎች የተሻለ መነቃቃት የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚታገለውን ሃይል ማነቃቃት ያኮራ፤ ይህም ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም