ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሠራተኞች ችግኝ ተከሉ

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አመራር አባላትና ሠራተኞች ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳረፉ።

ሠራተኞቹ ለአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በቢሸፍቱ ከተማ ልዩ ስሙ ኪዳንምህረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ተራራ ከ2 ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ተክለዋል።

በዚህም ከሰባት መቶ በላይ የድርጅቱ አመራር አባላትና ሠራተኞች ችግኝ በመትከል አሻራቸውን እንዳኖሩ ድርጅቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመላክቷል።

የድርጅቱ የግዥ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ግርሻ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብርን የለውጥ ሥራዎች አካል ሆኗል።

የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት ተጠናቆ ቀጣይ ሥራዎች እየተከናወኑ ባለበት ወቅት መሆኑም አውስተዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ድርጅቱ የሚተክላቸውን ችግኞችን በየዓመቱ እየተንከባከበ መሆኑን ነው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሠራተኞች ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰባት ሺህ ችግኞችን መትከላቸውን መግለጫው ገልጿል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጭነት በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የ2013 ዓ.ም መርኃ ግብር "ኑ ኢትዮጵያን እናልብስ" መሪ ሃሳብ በመላው አገሪቷ እየተካሄደ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ ዓለምን እየፈተነ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ለመቋቋምና የሥርዓተ-ምህዳር ሚዛን አስጠብቆ ለመሄድ እንደሚረዳ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም