በትራፊክ ማስተናበር የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በመሳተፋቸው በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረን አደጋ ቀንሷል - ኢዜአ አማርኛ
በትራፊክ ማስተናበር የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በመሳተፋቸው በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረን አደጋ ቀንሷል
ነሀሴ 9/2013 (ኢዜአ) የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በትራፊክ ማስተናበር ስራ ላይ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረ አደጋ መቀነሱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለጸ።
ቢሮው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመሆን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኢንጅነር ብርሃኑ ግርማ እንዳሉት፤ የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በትራፊክ ማስተናበር ስራ ላይ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በተሽከርካሪ ይደርስ የነበረ አደጋ ቀንሷል።
በተሽከርካሪ አደጋ የሚጠፋውን የሰው ልጅ ሕይወትና የኢኮኖሚ ኪሳራ ለመቀነስ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበኩሉን አስተዋጾ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
''በበጎ ፈቃድ የሚሰራው ስራ ለራሳችንና ለወገናችን ነው'' የሚሉት ኢንጅነር ብርሃኑ፤ ሁሉም ለስራው ትብብር ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል።
ካለፈው አራት ዓመት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመሆን በ2009 ዓ.ም በ100 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የተጀመረው ስራ በየጊዜው ለውጥ እያሳየና ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይ ከእስጢፋኖስ እስከ መገናኛ ባለው መንገድ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤ ወጣቶቹ ከመግባታቸው አስቀድሞ ከነበረው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ወቅት ምንም አደጋ ያለማጋጠሙን ተናግረዋል።
በከተማ እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች በመስራት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት "በከተማዋ እያደገ መጥቷል" ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ ናቸው።
በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በተለያዩ ሙያዎች አገልግሎት ላይ እየተሳተፉ ነው።
ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚውል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ ችለዋል።
በዚህ ዓመት በበጎ ፍቃድ ስራው ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች ለማሳተፍ ታቅዶ ከሶስት ሚለዮን በላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የክረምት በጎ ፍቃድ ስራ ከተጀመረ ሁለት ወራት እየተጠጋው ሲሆን፤ እስከ አሁን በ19 መርሃ ግብሮች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰራ ይገኛሉ።
በበጎ ፍቃድ ስራም ባለሀብቶች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በዚህም "ውጤታማ ስራዎች እየተሰራ ናቸው" ብለዋል።
በበጎ ፍቃድ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በበኩላቸውን፤ በበጎ ፍቃድ ስራ በመሰማራት ሰዎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ በማድረግ የሚያስደስት ጉዳይ ነው።
ወጣት እመቤት ዘውዴ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የምትሰጥ ሲሆን፤ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰትና በሰውም ህይወት በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር በጋራ በመስራት የተሻለ ውጤት መገኘቱን ትገልጻለች።
ወጣት ይታገሱ አሰበ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊ እንደምትለው፤ ወጣቶች በሚሰጡት ትራፊክን የማስተናበር ስራ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሰዎች ናቸው።