ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ሰላም መረጋገጥ በሽብርተኞች ላይ የዘመተው መከለካከያ ሠራዊትን እናግዛለን - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ሰላም መረጋገጥ በሽብርተኞች ላይ የዘመተው መከለካከያ ሠራዊትን እናግዛለን
አሶሳ ነሐሴ 09 / 2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የአገር መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ አብዱልሙኒዬም አደም ገለጹ።
የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ዛሬ በአሶሳ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ እየተዋጋ ያለውን ሠራዊት በሁለንተናዊ መልኩ መደገፍ ይገባል።
''የአገር ደህንነትና ልማታችን በዘላቂነት የሚረጋገጠው ቡድኑ ከነተላላኪዎቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ መቃብር ሲወርድ ብቻ ነው'' ብለዋል።
ህብረተሰቡ ሠራዊቱን ለማጠናከር ድጋፉን ማጠናከር ይጠበውበታል ብለዋል።
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡመር መሐመድ የአሸባሪው ቡድን ርዝራዦች ተልዕኮ ተቀብለው እየተሯሯጡ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት ተወካይ ሻለቃ መከተ ኑረዲን አገር ሠላም እንድትሆን ሁሉም አካባቢውን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
''አገር አፈርሳለሁ የሚለው ጁንታው ራሱ ይፈርሳል እንጂ፤ እኛ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም'' ብለዋል፡፡
የማስ ስፖርት አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሄለን ሃይሉ ''ሠላም ከሌለ ህዝብ መኖር አይችልም፡፡በመሆኑም ሃገራችን ከህወሃት ጥፋት ለማዳን እንዘምታለን'' ብላለች፡፡
ወይዘሪት ምርቴ ምትኩ በበኩሏ የሃገር መከላከያ ሠራዊት የአገር መከታ እንደሆነ ገልጻ፤ ደመወዟን ለአገር መከላከያ ሠራዊት በድጋፍ መስጠቷን ትናገራለች፡፡
እንዲሁም ስንቅ በማዘጋጀትና ደም ለመለገስ ድጋፍ ማድረጓን ገልጻለች፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የስፖርት ማህበረሰብ ለአገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነቱን ያሳየበት መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።