ቀጥታ፡

የግልገል በለስ ከተማ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሠላም ለመጠበቅ ተዘጋጅተዋል

ነሐሴ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሚያሰማራቸው ሽፍቶች የአካባቢያቸውን ሠላም እንዳያደፈርሱና የሕዳሴ ግድብ ግንባታን እንዳያደናቅፉ ነቅተው እንደሚጠብቁ የግልገል በለስ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
 የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት ያቀረበውን ጥሪ የተቀበሉ የግልገል በለስ ከተማ ወጣቶች ወደ ሕዳሴ ግድብ የሚጓጓዙ ንብረቶችን ደህንነት ለመጠበቅ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለአፍታም ቢሆን የግድቡ ግንባታ መቆም የለበትም ያሉት የከተማዋ ወጣቶች ከጸጥታ ሃይሉ ጎን ተሰልፈው የአካባቢያቸውን ሠላም ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በማዕረግና በተለያዩ የስራ ሀላፊነቶች ሲያገለግሉ ቆይተው በክብር በተሰናበቱ አባላት የሚመሩ በመቶ፣ በሻምበልና በሻለቃ አደረጃጀት ለተዋቀሩ የከተማዋ ወጣቶች ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።

ወጣቶቹ ከተማዋ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ቁሳቁስ የሚተላለፍባት እንደመሆኗ አሸባሪው ህወሓት የሚያሰማራቸው ሽፍቶች የግድቡን ግንባታ እንዳያስተጓጉሉ ከጸጥታ ሀይሉ ጎን ተሰልፈው የአካባቢውን ሠላም እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።

"የሕዳሴው ግድባችን ስራ ለደቂቃም ቢሆን አይቆምም" ያሉት ወጣቶቹ' የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በስልጠና ማስጀመሪያው ላይ ያገኘነው ወጣት አዘዘው ዘውዱ እንዳለው እናትና አባቶቻችን ምንም ሳይኖራቸው ያቆዩአትን አገር ወጣቶችም አስጠብቀን እንቀጥላለን ብሏል።

አሁንም አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል እስከመጨረሻው ለመፋለም ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል። 

ወጣት ዱፌራ አብደታ በበኩሉ የኢትዮጵያ ህልውና በሆነው በህዳሴው ግድብ የሚመጣን ማንኛውም ሃይል እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለመመከት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ለግድቡ ግንባታ ቁሳቁስ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎቸ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲጓዙ ተደራጅተው ጥበቃ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጿል።

ወጣቱ የአካባቢውን ሠላም በማስጠበቅ የልማት ስራዎች ተጠናከረው እንደሚቀጥሉ ሙሉ እምነት እንዳለውም ነው የገለጸው።

የዓባይን ግድብ የሚያስተጓጉል ምንም አይነት ሃይል ሊኖር አይገባም ያሉት ደግሞ  የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሃምሳ አለቃ ሞላ ምህረቱ ናቸው። 

እንደዚህ አይነት አደረጃጀቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው የመንገዱን ሠላማዊነት ለማረጋገጥ ለሚደረጉ ስራዎች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም