ከራሳችን ሕይወት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እናስቀድማለን - ኢዜአ አማርኛ
ከራሳችን ሕይወት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እናስቀድማለን
ነሀሴ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከሕይወታችን በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እናስቀድማለን፤ አገር ያቀረበችልንን ጥሪ ተቀብለን ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን ለማስከበር ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ገለጹ።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን መጠበቅ አለበት ያሉት አባላቱ ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተሰባስበው ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን በመግለጽ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን አውግዘዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በባለፈው ሣምንት ባወጣው መግለጫ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና ስጋት ዜጎች በጋራ እንዲመክቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።
የቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላቱም የቀረበውን አገራዊ ጥሪ በደስታ እንደሚቀበሉት፤ የኢትዮጵያ ሕልውናና ዳር ድንበር ለማስጠበቅም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በቀረበላቸው አገራዊ ጥሪ መሰረት ባላቸው አቅም ድጋፋቸውን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል።'የቀድሞው ሠራዊት የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው' ያሉት አባላቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ መስዋዕት መክፈሉን፤ አሁንም አገሩን ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን ነው አባላቱ የገለጹት።
አገር ለማፍረስ የተነሳው የህወሓት ቡድን ያሰበው እንደማይሳካለትና ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያን እንደሚያስቀድሙ ተናግረዋል።"ሁሉም የሚኖረው ኢትዮጵያ ስትኖር ነው" ያሉት የቀድሞ ሠራዊት አባላት ሁሉም ዜጋ አገሩን መጠበቅ አለበት ብለዋል።ሕዝቡ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በአንድነት በመቆም የህወሓትን የሽብር ቡድን ሴራ ማክሸፍ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።
የቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ ባደረጉት ሠላማዊ ሠልፍ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቀድሞ ጄኔራሎችና ከፍተኛ አመራሮች፣ የቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦች ታድመዋል።በርካታ ኢትዮጵያዊያን "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ" የትም፣ መቼም፣ በምንም በሚል ለቀረበው አገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የመከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ላይ ናቸው።