ቀጥታ፡

በተማርንበት ሙያ ህዝባችንን ለማገልገል ዝግጁ ነን

ነቀምቴ፣ ነሐሴ 09/2013(ኢዜአ)  በተማሩበት ሙያ ህዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ተናገሩ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች ያስተማራቸውን ከ5ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን ለ16ኛ ጊዜ አስመረቀ፡፡

በምረቃው ስመስረአቱ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች ታዲያ ጠንክረው ለእለቱ መድረሳቸው እንዳስደሰታቸው ነው የተናገሩት።

በተማሩበት የሙያ መስክ ያስተማራቸውን ሕዝብ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት ተማሪዎቹ በተለይም በአሁኑ ወቅት አገራቸው ብዙ ነገር የሚትጠብቅባቸው በመሆኑ ሁሉም ተመራቂ ለአገሩ የአቅሙን ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል የሆልቲ ካልቸር የትምህርት ክፍል የዋንጫ ተሸላሚ ተማሪ አማኑኤል ደረጀ ትምህርቱን ጠንክሮ በመስራቱ የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን ተናግሮ ለወደፊቱም ለሕዝቡ ችግር ፈቺ የሆነ የጥናትና ምርምር ሥራ በማካሄድ ሕብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በእንስሳት ሕክምና የትምህርት ክፍል የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ተመራቂና የሁለት ሜዳሌያ ተሸላሚ ተማሪ ገላኔ አብዲሣ በበኩሏ በተማረችው የሙያ መስክ ያለመታከት በመስራት ሕዝቧን ለማገልገል መዘጋጀቷን አስረድታለች፡፡

ሌላው የደቡብ ሱዳን ዜጋና የሳይኮሎጂ የትምህርት ክፍል ተመራቂና የሜዳሌያ ተሸላሚ ቶል ቱዲሪክ በበኩሉ በሙያ አገሩን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሰብዕናን በመላበስ አፍሪካን ጭምር ለማገልገል መዘጋጀቱንና የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ የደቡብ ሱዳንን ሥደተኞች በመቀበል እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግኗል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የግምቢ እና የሻምቡ ካምፓሶችን ጨምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለ16ኛ ጊዜ በመደበኛ፣ በተከታታይና በርቀት የትምህርት ፕሮግራሞች በቅድመ ምረቃ 5 ሺህ 359፣ በሁለተኛ ዲግሪ 550፣ እንዲሁም በሶስተኛ ዲግሪ ደግሞ 8  በአጠቃላይ 5 ሺህ 903 ተማሪዎችን ማስመረቁን አስታውቀዋል፡፡

የዕለቱ ተመራቂዎች ለአገሪቷ ሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ በተመረቁበት የሙያ መስክ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ተመራቂዎችን ማስመረቅ በመቻሉ ከፍተኛ ደስታ ይሰማዋልም ብለዋል ዶክተር ሀሰን።

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የዕለቱ ተመራቂዎች በሕብረተሰቡ ውስጥ ድርሻቸው ምን እንደሆነ በሚገባ ተረድተው፤ ያስተማራቸውን ሕዝብ በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

የወለጋ ዪኒቨርሲቲ ከ2001 እስከ 2013 ዓ.ም 66 ሺህ 141 ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉንና በአሁኑ ጊዜ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የሙያ መስኮች በማስተማር ላይ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም