ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ለደቀነውን ወቅታዊ ችግር ወጣቶች የሰጡት ፈጣን ምላሽ የሚደነቅ ነው

ነሐሴ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ለደቀነውን ወቅታዊ ችግር ወጣቶች የሰጡት ፈጣን ምላሽ የሚደነቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌዴሬሽኑ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ኤርሚያስ ማቲዎስ እንደገለጸው፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለመፈራረስ የውክልና ጦርነት እያደረገ ይገኛል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ቡድኑ የተዛቡ መረጃዎች ሲያቀርብ እንደነበር አስታውሶ፤ “ግድቡ ተሸጧል፣ እኛ ካልመራናችሁ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ ህገመንግስት አልተከበረምና መሰል ሃሰተኛ ፕሮፓንጋንዳ ሲያሰራጭ ነበር” ሲል ለአብነት አንስቷል።

በዚህ ያላበቃው ቡድኑ የአገር መከለከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ክህደቱንና አገር አፍራሽነቱን በግልጽ ማሳየቱን ገልጾ፤ “በዚህ ወቅታዊ ችግር ወጣቱ ወደ ጦር ግንባር ከመዝመት ጀምሮ       ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርገዋል” ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ጫናውን በመቃወም ያሳዩት ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ተናግሯል።

በዚህም ወጣቶች ለሀገራቸው ልዑላዊነት መከበር ያሳዩት ንቁ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጽጌረዳ ዘውዱ በበኩሏ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ጫናው ከየትኛው ጊዜ በላይ የበረታበት መሆኑን ተገንዝበው አገርን ለማፍረስ የመጣውን ተላላኪና ለመመከት ያሳዩትን አገር ወዳድነት እንዲያጠናክሩ ጠይቃለች።

ወደ ግንባር ያልሄዱ ወጣቶች ለዘማች ቤተሰቦች የግብርና ቦታው በመንከባከብ ጨምሮ የተለያዩ ተግባር በመስራት ደጀንነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው አመላክታለች።

ወጣቶች የአሸባሪውን ህወሓት ተግባርና የሀሰት ፕሮፓንጋዳ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅና ጫና ለመፍጠር     መስራት እንዳለባቸውም ገልጻለች።

ከዚህ በተጨማሪ አሸባሪው ህወሓት የሚፈፅመውን ጭፍጨፋና ህጻናት ወደ ጦር ግንባር በመላክ የሚጸፍመው ወንጀል መቃወምና እውነቱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ስራ ከወጣቶች እንደሚጠበቅም አብራርታለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም