ቀጥታ፡

በአገራችን ዳር ድንበር ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን በጋራ እንመክታለን

መተማ  ነሃሴ 8/2013  (ኢዜአ) የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመመከት ተዘጋጅተናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ ወጣቶች ገለጹ።

በከተማዋ ለ15 ቀናት መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ የከተማዋ ወጣቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ዛሬ ሲመረቁ እንደተናገሩት በአገር ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የሚደረግ ድርድር የለም።

ከተመራቂዎቹ መካከል ወጣት አባይነህ አስቻለው እንደተናገረው የተሰጠው መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና አካባቢውን ብሎም አገሩን ከጥቃት መከላከል እንዲችል የሚያደርግ ነው።

''ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና ሁሉም ህብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት አገሩን በአሸናፊነት እንድትወጣ ማድረግ ያስፈልጋል'' ያለው ወጣቱ በየትኛውም ግንባር በመሰለፍ ጠላትን ለመመከትና ለመደምሰስ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የህዝብን ሰላምና ደህነንት አደጋ ላይ ሊጥል የሚመጣን ኃይል በመጣበት መንገድ ለመመለስና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ስልጠና ወስዶ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ሌላኛው ሰልጣኝ ወጣት አለበል አዲሱ በበኩሉ ''ኢትዮጵያ በየትኛውም አውደ ውጊያ ተሸንፋ እንደማታውቅ ታሪክ ምስክር ነው'' ብሏል።

ህዝቡና መንግስት እውነትን ይዞ ወደ ፊት በመሄድ በሃገሪቱ ህልውና ላይ አደጋ የጋረጡ ጠላቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ይገባል ነው ያለው።

የሀገሪቱ ፈጣን የለውጥ እርምጃ በቀጣይ ሊኖራት የሚችልን ተፅዕኖ ፈጣሪነት አስቀድሞ ያሳየ በመሆኑ ይህ እንዲሆን የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች በሚያደርጉት ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የተንኮል ሴራን በህዝቦች አንድነት ማክሸፍ ይግባል።

''ባገኘሁት ስልጠና ሀገሪቱ የተደቀነባትን አደጋ ለመቀልበስ ዝግጁ ነኝ'' ያለው ደግሞ ወጣት ዮሃንስ ጌታቸው ነው።

በሀገሪቱ ደካማ መንግስት እንዲመሰረት የሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች የኢትዮጵያን ህዝብ ስነልቦና በአግባቡ ያልተረዱ መሆናቸውን ገልጿል።

ምዕራባውያን ጣልቃ የገቡባቸው ሀገራት ፈራርሰው በተድላና በደስታ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦቻቸውም ለስደት ተዳርገዋል ያለው ወጣቱ ኢትዮጵያ ላይ ይህ እንዲፈጠር የሚፈቅድ ትውልድ አለመኖሩን አረጋግጧል።

የገንዳ ውሃ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ይግለጥ አበባው በበኩላቸው የከተማዋ ወጣት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛና በጎ አድራጎት ግንባር ቀደም ተዋናይ በችግር ጊዜ ደግሞ የሀገር ዳር ድንበርን የሚያስከብር ነው ብለዋል።

ዛሬ ስልጠናውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በህልውና ዘመቻው በመሳተፍ ህዝቡ የገጠመውን የህልውና አደጋ መመከትና አሸባሪውን ቡድን ማጥፋት ግድ የሚልበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ባለፈው ጥቅምት 24 /2013 ዓ.ም ጁንታው በሀገር መከላከያ ላይ በፈጸመው ክህደት በነበረው ህግ የማስከበር ሂደት የከተማዋ ወጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከተማዋ የወደብ ከተማ በመሆኗና ከሱዳን በቅርብ ርቀት ስለምትገኝ ፀጉረ ልውጥ ሾልከው እንዳይገቡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተጠናከረ ክትትል ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ለህልውና ዘመቻው ስንቅና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የከተማዋ ማህበረሰብ እያደረገው ያለው ተሳትፎ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም