ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት የኪነ ጥበብ ተቋማትን በማፍረስ ኢትዮጵያዊነት እንዳይጎላ አድርጓል

ነሐሴ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሃት አገር ባስተዳደረባቸው ዓመታት የኪነ ጥበብ ተቋማትን በማፍረስ ኢትዮጵያዊነት እንዳይጎላ፣ መከፋፈል እንዲፈጠር ሲሰራ ቆይቷል።

ብሔራዊ የኪነ ጥበብ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የኪነ ጥበብ ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በየብሄረሰቡ መልከ ብዙ ባህላዊ የማጀገኛ ኪነ ጥበባት ይገኛሉ።

ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው ሰላምና ፍቅር ወዳድ በመሆናቸው ሌሎችን የመውረርና የማጥቃት ታሪክ እንደሌላቸው አንስተዋል።

ወረራና ጥቃት ሲፈጸምባቸው ግን በሕብረት መክተው ደማቅ ታሪክ መጻፋቸውን አውስተው፤ "ለዚህ ደግሞ በየማህበረሰቡ ያሉ ባህላዊ ከያኒያን ጠላትን ለመመከት ሃይልና ደጀን ሆነዋል" ብለዋል።

አገር ስትወረርና ሉዓላዊነቷ ሲደፈር ሙዚቃ፣ ግጥምና ሌሎች የኪነ ጥበብ ትሩፋቶች ማህበረሰቡን በማነቃቃትና ሠራዊቱን በማጀገን ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ነው ያብራሩት።

ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት በቀዳሚነት የሚነሳው የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት መስራች ከያኒያንም የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን ለመመከት አርበኞችን ለማጀገን፣ የመዋረድና የመሸነፍን ክፋትና የድልን ከፍታና ጥልቀትን ለማሳየት መሰባሰባቸውን ገልጸዋል።

"ሀገር ፍቅር ቴአትርን ጨምሮ በርካታ የኪነ ጥበብ ማዕከላትና አደረጃጀቶች ተቋቁመው የአገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊ አንድነትን እንዲጎላ ትልቅ ሚና ነበራቸው" ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ።

በደርግ አገዛዝ ወቅትም ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር የኪነት ቡድኖች ተቋቁመው ለባህል ዕድገትና አገራዊ አንድነት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አመልክተው፤ "በወቅቱ ድንቅና ዘመን ተሻጋሪ ድምጻዊያንም አፍርተዋል" ብለዋል።

የኪነት ቡድኖቹ የወቅቱን የኢትዮጵየ ነባራዊ ሁኔታ የገለጹ፣ ታሪክ የዘገቡና መጭውን የኢትዮጵያ መጻኢ እድል የተነበዩ እንደነበሩም አስረድተዋል።

"ነፃ አውጭ ነኝ በሚል" አደናግሮ ስልጣን ተቆናጦ የነበረው አሸባሪው ሕወሃት ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የኪነ ጥበብ ተቋማትን በስፋት የማክሰም ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

"አሸባሪው ህወሃት ላልይበላ፣ ፋሲለደስና ግሽ አባይ በሚል ይታወቁ የነበሩ ኪነት ቡድኖችን በማፍረስ የኪነ ጥበብ ጠንቅ መሆኑን አሳይቷል" ብለዋል።

ከያኒያን በነጻነት እንዳይሰሩ በማድረግ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ሲደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የውጭ ሃይሎች በአድዋ ድል የተሸነፈው እሳቤያቸውን የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት በማሳሳትና በማፍረስ መበቀል እንደሚሹ ገልጸው፤ በዚህም የጭቆና ትርክትን በማነሳሳት ከፋፋይ ጥበባዊ ስራዎች እንዲሰሩ መደረጉን አብራርተዋል።

'አሁን አሁን እኛ ኢትዮጵያዊያን አይደለንም' የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በኪነ ጥበቡ የተስተዋሉትም ሀሰተኛ የጨቋኝ፣ ተጨቋኝ ትርክት መነሻነት እንደሆነ አብራርተዋል።

በአሸባሪው ሕወሃት ዘመንም ቢሆን በጫና ውስጥ ሆነው የጥበብ ምሽቶችን በማዘጋጀትና በሌሎች ጥበባዊ ስራዎች ኢትዮጵያዊነት ያቀነቀኑ ከያኒያን እንደነበሩ ገልጸዋል።

በዚሁ ወቅት ኪነ ጥበብ ለአገር አንድነት የነበራትን ሚና በመረዳት በአሸባሪው ሕወሓት ዘመን የነበረውን ጫና በማንሳት፣ ከያኒን በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ምቹ ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም ከያኒያን እንደ የጥበብ ዘርፋቸው በአገራቸው ታሪክ እንዲያወሱ፣ ነገን እንዲተነብዩ በነጻነት የሚንቀሳቀሱ የኪነት ማዕከላት ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ክብሯና አንድነቷ ተጠብቆ ለተረካቢ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም በያለበት የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም