በሀገር ላይ የሚቃጣ እኩይ ተግባር ለመመከት ዝግጁ ነን - የጋምቤላ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ላይ የሚቃጣ እኩይ ተግባር ለመመከት ዝግጁ ነን - የጋምቤላ ወጣቶች
ጋምቤላ ፤ነሐሴ 8/2013 (ኢዜአ) በሀገር ህልውና ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም እኩይ ተግባር ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን የጋምቤላ ክልል ወጣቶች አስታወቁ።
"ግድቡ ለወጣቱ ወጣቱ ለግድብ ’’በሚል መሪ ሃሳብና ሌሎች ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ መልዕክት የተላለፈበት የወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።
በሰልፉ ላይ የኢትዮጵያ ትንሳኤ በህዳሴው ግድብ ይረጋጣል፣ግድቡ የእኛ ነው፣ እኛ ወጣቶች ያለን እውቀትና አቅም ለሀገራችን ልማት እናውላለን! ወጣቶቹ ካስተላለፏቸው መልዕክቶች ይገኙበታል።
ከሰልፉ ተካፋዮች መካከል ወጣት ኮንግ ጋድቤል ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሀገር ህልውና ላይ የሚቃጣ እኩይ ሴራን ለማክሸፍ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ወጣት ኮንግ፤ አሁን ላይ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ከሀገር መከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር ለመሰለፍምና ለመመከት ተነሳስቷል።
ሰልፍ ያካሄዱት የታለቁ የህዳሴ ግድብናና ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ ስኬት ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ነው ያለው ደግሞ ወጣት ሉዋል ኡሞድ ነው።
እንደ ጋምቤላ ወጣት ለግድቡም ሆነ ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሰለፍ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱን ነው ያረጋገጠው።
የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ኡችዎድ ባች በሰልፍ ላይ ባደረገው ንግግር፤ አሁን ላይ በውስጥና ውጭ ጠላቶች የተደቀነውን ፈተና በድል ለማሻግር በሚደረገው ጥረት የክልሉ ወጣቶች በነቃት ለመሳተፍ መሰናዳታቸውን አስታውቀዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በድል እንደተጠናቀ ሁሉ የተጀመረውም የህልውና ዘመቻ በስኬት ከፍጻሜ እንዲደረስ እንሰራል ብሏል ወጣት ኡችዎድ።
የውስጥና ውጭ ኃይሎች የህዳሴውን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማደናቀፍ ያደረጉት ሙከራ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና በክልሉ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተንኳይ ጆክ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን አንድ ከሆንን የማንሻገረው ፈተና አይኖርም ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፤ አሁን ላይ የትህነግ አሸባሪ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ የክልሉ ወጣቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሸን አባላትና የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት ሪፖርተር ከስፍራው ዘገቧል።