ከደመወዝና ደም ልገሳ ባለፈ በሁሉም ነገር ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ነን - ኢዜአ አማርኛ
ከደመወዝና ደም ልገሳ ባለፈ በሁሉም ነገር ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ነን
ደብረ ብርሃን፣ ነሐሴ 7/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ሰራተኞች በጦር ግንባር ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ከደመወዝና ደም ልገሳ ባለፈ በሁሉም ነገር ከጎኑ መሆናቸውን እየገለጹ ነው።
የባለስልጣኑ ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለሰራዊቱ አበርክተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎ እንደገለፁት አሸባሪው የህውሃት ቡድን በአገሪቱ እያደረሰ ያለውን ሃገር የማፍረስ ተልእኮን ለመመከት የባለስልጣኑ ሰራተኞች ዝግጁ ናቸው ።
በአፋር ክልል በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ግድያ እና በአማራ ክልል የሚያደርገው ወረራና ዘረፋ እንዲሁም የዜጎች መፈናቀል የቡድኑን የአሸባሪነት በግልፅ ያሳየ ነው ብለዋል።
በአጥንትና በደም የተገነባችውን ሀገር የሚያፈርሳት አንድም ሃይል የለም ያሉት ዳይሬክተሩ ሃገራችን የገጠማትን ስብራት ለመጠገን እንሰራለን ብለዋል ።
ለዚህም የባለስልጣኑ ሰራተኞች ከነሐሴ ወር 2013 ዓ/ም ጀምሮ የሚከፈል የአንድ ወር ደመወዛቸውን 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በድጋፍ ማበርከታቸውን ጠቅሰው፤ የችግኝ ተከላና ደም ልገሳ ማከናወናቸውንም ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍረታና ግድም ወረዳ በአጣየ ከተማ በጽንፈኛ ሃይሎች የደረሰውን ጉዳት ለመደገፍም 200 ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም አመልክተዋል።
የደብረ ብርሃን ደም ባንክ ሃላፊ አቶ ክፍሌ ክፈተው በበኩላቸው ህዝብ ለህልውና ዘመቻው የሚደረገው የደም ልገሳ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።
በዚህም ከሐምሌ ወር 2013 ዓ/ም ጀምሮ በተካሄደ ደም የማሰባሰብ እንቅስቃሴ 998 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቀደኛ ደም ለጋሾች መሰባሰቡን ተናግረዋል።
ዛሬ ላይ የባለስልጣኑ ሰራተኞች ደብረ ብርሃን ድረስ መጥተው ደም መለገሳቸውም ለሃገራዊ ጥሪው ለወገናቸው ያላቸውን ድጋፍ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የባለሰልጣኑ ሰራተኞች አቶ ቢኒያም ለገሰ በበኩላቸው ህውሃት ሃገራችንን ለመበታተን ከውጭ ሃይሎች ጋር የሚያሴረውን ሴራ ለማከሸፍ መንግስትን መደገፍ ይገባል ብለዋል።
የመንግስትን ጥሪ በመቀበልም ለመከላከያ ሰራዊት ካደረጉት የገንዘብና የደም ልገሳ ጎን ለጎን በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ ለመሆን ትግሉን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ምህረት ግርማ በበኩላቸው የሃገርን ክብር የማይገባው እርካሽ ቡድን ለመደምሰስ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ደብረ ብርሃን መምጣታቸውም የአማራ ክልል ህዝብ በዋነኛነት በወቅታዊ ችግር ውስጥ ያለ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ ጎን መሆናችንን ለመግለጽ ነው ብለዋል።