ቀጥታ፡

አንዳችን ለሌላችን ወታደር ሆነን አገርን ለማፍረስ የሚደረጉ ከንቱ ቅዥቶችን እስከ መጨረሻው ማጥፋት ይጠበቅብናል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን አንዳችን ለሌላችን ወታደር ሆነን አገርን ለማፍረስ የሚደረጉ ከንቱ ቅዥቶችን እስከ መጨረሻው ማጥፋት ይጠበቅብናል።

አሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ በይፋ "ትብብር ፈጥረናል" ማለታቸው በድብቅ ሲያከናውኑት የቆየው አገር የማፍረስ ተልዕኮ በመክሸፉ ተስፋ መቁረጣቸውን እንደሚያመላክትም ነው የተገለጸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያዚያ 2013 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “ሕወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።

የሽብር ቡድኖቹ ቀደም ሲልም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት፣ ግድያና መፈናቀል እንዲከሰት በማድረግ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በስውር ተቀናጅተው ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል።

ከቀናት በፊት ደግሞ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ኢዜአ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን በሚመለከት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደዓ እና ከፍልስፍና ምሁሩ አቶ ዮናስ ዘውዴ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አቶ ታዬ ደንደዓ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በመራባቸው 27 ዓመታት በየትኛውም የአገሪቱ ጥግ በሚኖሩ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግፍ ሲፈጽም ቆይቷል።

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መስዋዕትነት በመክፈል የአሸባሪው ህወሃት የአፈና አገዛዝ እስከ መጨረሻው እንዳሰናበቱትም ነው ያስታወሱት።

የሽብር ቡድኑ "ሸኔ" የሚባለውን ስብስብ የአፈና አገዛዙን ለመመለስ እንደ ጭንብል እየተጠቀመበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ታዬ፤ ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት "ሸኔ ናችሁ" በሚል የኦሮሚያ ወጣቶችን ሲያሰቃይና ጥፍር ሲነቅል መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን አስረድተዋል።

በድብቅ በማስታጠቅም የኦሮሞ ህዝብ ላይ ግፍ እንዲፈጸም ሲያደረግ መቆየቱንም አብራርተዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ በይፋ "አብረን እንሰራለን" በማለት ማወጃቸው በድብቅ ሲያከናወኑት የቆዩት አገር የማፍረስ ተልዕኮ ባለመሳካቱ ተስፋ መቁረጣቸውን እንደሚያመላክት አስረድተዋል።

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞ ወጣቶችን ሲገድልና አካል ሲያጎድል ከነበረው አሸባሪው ህወሃት ጋር ትብብር መፍጠሩ የቡድኑ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ ለኦሮሞ ህዝብ መብት የቆመ ድርጅት አለመሆኑን በተግባር ማስመስከሩን ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ወጣቶች የህወሃት ግፍ አንገሽግሿቸው ወደ ጎዳና ሲወጡ "አሸባሪው ሸኔ የሚባለው ስብስብ የት ነበር፤ ይህም የሁለቱን የሽብር ቡድኖች የቀደመ ጋብቻ ያሳያል" ነው ያሉት።

በመሆኑም "የሽብር ቡድኖቹ አሁን ላይ በይፋ በጋራ እንሰራለን ማለታቸው አዲስ ጉዳይ ባይሆንም ለኦሮሞ ህዝብ ግን  የማንቂያ ደወል ነው" ብለዋል።

የፍልስፍና ምሁሩ አቶ ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አገር ሳንፈልገው የምናፈርሰው ስንፈልገው የምንገነባው ቀላል ጉዳይ አይደለም።

የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያሳየው ደግሞ "ኢትዮጵያዊያን በአገር ህልውና ላይ አደጋ የሚጥል ጠላት በበዛ ቁጥር ይበልጥ በጋራ እንደሚቆሙ ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁሉም ነገር ከሀገር በታች መሆኑን ያስተማሩ ቀደምት ህዝቦች መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።

ልማት ብልጽግና እንዲሁም ክብር የሚለው ጉዳይ እውን የሚሆነው ሀገር ጸንታ ስትቆም መሆኑን የገለጹት አቶ ታዬ ደንደዓ  በሁሉም ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ ዘወትር መታሰብ እንዳለበት ይናገራሉ።

ሀገር ከሚጸናባቸው ጉዳዮች ደግሞ የጸጥታ ተቋማት ዋነኞቹ መሆኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያውን ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ ሠራዊት ደጀን መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

እያንዳንዱ ዜጋ ያለምንም መዘናጋት አካባቢውን በንቃት መቃኘት እንዳለበትም ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያን የማይፈልጉ ጠላቶችን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያንን የማድረግ አቅም መመልከት ተገቢ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ዮናስ ዘውዴ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን አንዳችን ለሌላችን ወታደር በመሆን "ሀገርን እስከ መጨረሻው የምናጸናበት ጊዜው አሁን ነው" ያሉት አቶ ዮናስ፤ ከዚህ አኳያ እያንዳንዳችን ለሀገር ህልውናና ክብር መስዋእት ለመሆን ጭምር ቁርጠኛ መሆን ይገባል ነው ያሉት።

ምእራባውያን እውነትን ካለማወቅ ሳይሆን እውነትን ለማወቅ ካለመፈለግ ወገንተኝነትን እያሳዩ መሆኑንንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም