የአርብቶአደር አካባቢዎችን የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርግ ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርብቶአደር አካባቢዎችን የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርግ ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 የአርብቶአደር አካባቢዎችን የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርግ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ በመጪው ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ። የፌዴራልና የአርብቶአደር ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ፍኖተ-ካርታው የአካባቢውን እምቅ የውሃና የእንስሳት ኃብት ለመጠቀም የሚያስችል ነው። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለፁት የአርብቶአደር አካባቢዎች ሰፊ የተፈጥሮ ኃብት መገኛ ቢሆኑም እስካሁን አገሪቱ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ላይ አላዋለችውም። ፍኖተ-ካርታው የግል ባለሃብቶችን በመስኖና በእንስሳት ኃብት ልማት ኢንቨስትመንት በማሰማራት አርብቶአደሮቹም፣ አገሪቱም እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያለመ ነው። በመሆኑም በአካባቢዎቹ ያሉትን ሁኔታዎች በማጥናት ለ10 ዓመታት መከናወን ያለባቸውን የትኩረት ነጥቦች በመያዝ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በእንስሳት ኃብት ''በአፍሪካ ቀዳሚ በዓለም 10ኛ ናት'' ከሚለው ቁጥር የዘለለ አርብቶአደሮቹም ሆነ አገሪቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተሰራው ስራ አናሳ እንደሆነ ገልጸዋል። ዝግጅት ላይ ያለው ፍኖተ-ካርታ መንግስት ለአካባቢዎቹ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥና መሟላት ያለባቸውን መሰረተ ልማቶች በሟሟላት የግል ባለሃብቶች በግብርና ማቀነባበሪያ ስራዎች እንዲሳተፉ ያደርጋል ነው ያሉት። ሚኒስትር ዴኤታው የፍኖተ-ካርታው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በ2007 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሠረት በአገሪቱ ከ56 ነጥብ 71 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብቶች፣ 29 ነጥብ 33 ሚሊዮን በጎች፣ 29 ነጥብ 11 ሚሊዮን ፍየሎችና 1 ነጥብ 16 ሚሊዮን ግመሎች ይገኛሉ፡፡