ቀጥታ፡

በአሜሪካ የሚኖሩ የቅማንት ተወላጆች ለህልውና ዘመቻው የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

ጎንደር ኢዜአ ነሐሴ 7/2013 ዓ/ም በአሜሪካ የሚኖሩ የቅማንት ተወላጆች አሸባሪው የህወሃት ቡድን የከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ ለተጀመረው የህልውና ዘመቻ ከ351ሺ ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን የጎንደር ከተማ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ባለሀብቶችና የመንግስት ሰራተኞች በህልውና ዘመቻው በግንባር ለሚዋደቀው የሀገር መከላከያ የልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የስንቅ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኛቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት ተወላጆች ሽብርተኛው ቡድን በሃገራችን ብሎም በአማራ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ እንዲቻል የገንዘብ ድጋፉን አበርክተዋል፡፡

የገንዘብ ድጋፉ የአማራና የቅማንት ህዝቦች የተዋለዱና የተዛመዱ አንድ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን እንዲሁም ወራሪውና አሸባሪው የህወሃት ቡድን የጋራ ጠላት መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ መናገራቸውን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

ተወላጆች ያሰባሰቡትን የገንዘብ መዋጮ ለወቅታዊ ሰላምና ደህንነት ማስከበሪያ ድጋፍ ለማሰባሰብ በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር በትናንትናው እለት በተወካያቸው በኩል ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የቅማንት ማህበረሰብ የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ ከአማራ ልዮ ኃይልና ሚሊሻ አባላትና ከህዝቡ ጎን በመሆን አሸባሪውን የህወሃት ቡድን የፈፀመውን ወረራ ለመቀልበስ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና የመንግሰት ሰራተኞች ለህልውና ዘመቻው የሚውል ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን በእብሪት ተነሳስቶ የጀመረውን ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራ ለማክሸፍ ህዝቡ እያደረገ ካለው የገንዘብና የስንቅ ድጋፍ በተጨማሪ ደም በመለገስና ልጆቹን መርቆ ወደ ግንባር በመላክ ጭምር ህዝባዊ አጋርነቱን እየረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም