ከጥፋቱ ለማይታረመው አሸባሪ ቡድን ጊዜ መስጠት አይገባም - ኢዜአ አማርኛ
ከጥፋቱ ለማይታረመው አሸባሪ ቡድን ጊዜ መስጠት አይገባም
ሰመራ ነሐሴ 7 ቀን 2013(ኢዜአ).አቶ መሐመድ አህመዲን የ75 ዓመት ባለፀጋ በአፋር ክልል የሰመራ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ "የአፋር ተንቀሳቃሹ የታሪክ፣ባህልና ቱሪዝም ቤተመጻህፍት"ወይም ''የአፋር ቱሪዝም አባት'' በመባል ይታወቃሉ።
የአፋርን ቱሪዝምና ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት ሰመራን የረገጡ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወይም በአገር አቀፍ መድረኮች ለሚታደሙ ሰዎች እርጋታ በተሞላበት ጥልቅ የማስረዳትና የመግለጽ ችሎታቸው ያስደምማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በአገራቸው ብሎም በክልላችው ጉዳይ ሲያነጋገራቸው ያካፈሉት ዕውቀት ጥልቅ ነው።ትናንትን ከዛሬ የሚያገናዝብ።የአገር ፍቅር ስሜትን ተላብሰው።
''አገር የተወሰኑ አመራሮች ወይም አካሎች ብቻ ሳትሆን፤ የሁሉም ዜጎች ናት።በመሆኑም የሁሉንም ንቁ ተሳትፎ ትፈልጋለች'' በማለት አቶ መሐመድ ገለጻቸውን ጀመሩ።
በተለይም እንደ አሁን "አገራችን እንደገጠመን ዓይነት በዴሞክራሲ ስም አገርና ሕዝብን ሲያደናግር ኖሮ፤ በሐሳብ የበላይነት ሲሸነፍ ውጤቱን አምኖ ለውጥ ራሱን ከማዘጋጀት ይልቅ፤ የተለያዩ እንቅፋቶችን ሲፈጥር መንግሥትና ሕዝብ በሆደ-ሰፊነት በትዕግሥት ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ይታረማል'' ተብሎ ሲጠብቀው ''የማይታረም'' ይሉታል አሸባሪውን ቡድን ትህነግን።
ቡድኑ በሂደት አካሄዱን ገምግሞ ከመታረም ይልቅ በስህተት ላይ ስህተት እየጨመረ አገሩን የከዳ፣ በስሜት እየተነዳ የትግራይን ሕዝብ ማብቂያ በሌለው ጦርነት በመማገድ ጦርነቱን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ማስፋፋቱ ንቀት ነው ይላሉ አዛውንቱ።
የአፋር ንጹሃን አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ሴቶችና ህጻናትን እንዲሁም አዛውንቶችን በከባድ መሳሪያ የገደለውና ለስደት የዳረገው ሽብርተኛ ቡድን መሳሳቱን የምናሳየው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነን 'አይቀጡ ቅጣት' በመቅጣት ነው ብለዋል።
በተለይም ወጣቶች ትህነግንና ተላላኪዎቹን አሳፍረው በመመለስ የአባቶቸቹ ተተኪ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።የዘመኑ አርበኛ እንዲሆንም አቶ መሐመድ መክረዋል።
እኔም ሰላም ለማስከበር ከሚተጋው ሃይል ጎን ነኝ ይላሉ።
''ከጡረታ አበሌ ቀንሼ አስተዋጽኦ አደርጋለሁ፤የአካባቢዬን ሰላምና ደህንነት እጠብቃለሁ፤ደምም እለግሳለሁ'' በማለትም በአገር ጉዳይ በንቃት እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
አቶ ዑመር ኢብራሂም የመንግሥት ሠራተኛና የሁለት ልጆች አባት ናቸው።
ሽብርተኛው ቡድን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የተካነው ሴረኝነት ሕዝብን መካከል ጥርጣሬና የጠላትነት ስሜት መፍጠር ልማዱ መሆኑን ያስረዳሉ።
የጥፋት ቡድኑ ወደ አፋር ክልልም በመምጣቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ በሕዝባችን ከማስከተሉም በላይ፤ በአገር ህልውና ላይ ጥቃት በማድረሱ አንታገሰውም ይላሉ።
በመሆኑም ተገደን በገባንበት ጦርነት የአገርን ህልውና የለማስጠበቅና ሠላምን ለማረጋገጥ፣የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን ለማክሸፍ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የአገር ሰላምና ጸጥታ ለሚስከብሩ ሃይሎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግና ካስለፈለገም የዘመቻው አካል በመሆን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ወይዘሮ ፋጡማ ጉራ የተባሉ ነዋሪ ተስፋ ቆርጦ አገር ለማጥፋት የተነሳውን ቡድን ከእኩይ ዓላማው ለመግታት ገንዘብ በማዋጣትና ስንቅ በማዘጋጀት እንደሚሳተፉ ይናገራሉ።ካስለፈለገም ሕይወታቸውን ይሰጣሉ።
በግል ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ዓሊ ሁሴን ዑመር በበኩሉ እንደገለጸዉ የአገሩን ዳር ድንበር ከውጭ ቀኝ ገዢዎች የጠበቀውና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራው የአፋር ክልል በአሸባሪው ትህነግ መደፈሩ እንደሚያገግባቸው ይናገራሉ።
"ሰንደቅ ዓላማችንንና ዳር-ድንበራችን እንኳን የአፋር ህዝብ ግመሎቻችንም ያውቃሉ"የሚባልበትን ክልል ልክ ያለማወቅም እንዳሳናቸው ይገልጻሉ።
የአፋር አርብቶ አደር ውድ ሕይወቱን እየከፈለ የአገሩን ዳር ድንበር በመጠበቅ ታሪካዊ አደራውን እየተወጣ መሆኑን ያለመረዳትም ማንነትን አለማወቅ ነው ይላሉ።
''እንደ አንድ ግለሰብ መንግሥት በአገር ህልውና ላይ የተጋረጠዉን ተጨባጭ አደጋ የመቀልበስ ተልዕኮ በአጭር ጊዜ በስኬት እንዲወጣ ከገንዘብ ድጋፍ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ብለዋል።
ከጥፋቱና ከስህተቱ የማይታረመውን የጥፋት ቡድን ማስተማሪያው መንገድ በመጣበት መንገድ መግጠም ሆኗል።የሰላምና እርቅ መንገዶችን ሁሉ ዘግቶ የመጣውን እብሪተኛ ድርጅት በመግታት ባልመረጥነው መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አመጣጡ ያርመዋል።''የማይታረመው''ን ለማረም እንገደዳለንና!