የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች በባህሬን ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች በባህሬን ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል
ነሀሴ 7/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የግብርና፤ የአግሮፕሮሳስንግና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች በባህሬን ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ፤ ንግድና ቱሪዝም ሚንስትር ገለጹ፡፡
በባህሬን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጽህፈት ቤት መሪ አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የኢንዱስትሪ፤ ንግድና ቱሪዝም ሚንስትር ሚስተር ዜይድ አልዜይን ጋር በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በዚህ ወቅት አምባሳደር ጀማል በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የህግና አሰራር ዙሪያ በተለይም በግብርና፤ በማኑፋክቸሪንግ፤ አግሮ ፕሮሳስንግ፤ በኤኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፤ በቱሪዝምና አገልግሎቶች መስክ ያሉትን ዕድሎች በተመለከተ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
የግብርና፤ የእንስሳት ተዋጽኦና የአግሮ ፕሮሳስንግ ምርቶች በባህሬን ገበያ በሚቀርቡበት ሁኔታ ላይ አምባሳደሩ ከሚኒስትሩ ጋር ተዋያይተዋል፡፡
አያይዘውም ሚስተር ዜይድ አልዜይን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
ሚስተር ዜይድ አልዜይን በበኩላቸው የሁለቱ አገራት የኢንቨስመንት፤ የንግድና የቱሪዝም ትስስር እንዲጠናከር እና የኢትዮጵያ የግብርና፤ የአግሮፕሮሳሲንግና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ወደ ባህሬን ገበያ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን እንዲጐበኙ የቀረበውን የግብዣ ጥያቄ በመቀበል የፈረንጆች አመት ከመጠናቀቁ በፊት ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ኢንቨስተሮችና የኩባንያ ኃላፊዎችን በመያዝ በኢትዮጵያን ጉብኝት ለማድረግ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡